የዜጎችን በነፃ ፍርድ ቤት የመዳኘት መብት ያከበሩ ተቋማትን ለመገንባት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

You are currently viewing የዜጎችን በነፃ ፍርድ ቤት የመዳኘት መብት ያከበሩ ተቋማትን ለመገንባት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

AMN- ሐምሌ 13/2017 ዓ.ም

የዜጎችን በነፃ ፍርድ ቤት የመዳኘት መብት ያከበሩ ተቋማትን ለመገንባት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህንፃና የዲጂታል አገልግሎትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለመንግስት አገልግሎት ሪፎርም ትኩረት ሰጥታ አየሰራች መሆኗን ያስታወሱት አቶ ተመስገን ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከልም በቴክኖሎጂ የታገዘ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች ብለዋል።

ዘመኑን በዋጀ መልኩ የታደሰው እና በቴክኖሎጂ የተደራጀው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትህ ሥርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን ለተቋም ግንባት ትኩረት መሰጠቱ የአመራሩን ጥንካሬ እንደሚያመላክት የጠቀሱት አቶ ተመስገን፣ በክልሉ በፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስና ግልጽና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የህግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር የፍርድ ቤቶች መዘመንና በቴክኖሎጂ መታገዝ ዘመኑ የሚያስገድደው ስራ ስለመሆኑ ያነሱት ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ናቸው።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አለምአንተ አግደው፣ የተቋሙ የቀድሞ ገፅታ ለስራ የማይመች እና የዜጎችን በግልፅ ችሎት የመዳኘት መብት ያላከበረ እንደነበረ አስተውሰዋል።

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው የለውጥ ስራ በተለያዩ የፍትሕ ተቋማት ላይም ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

በካሳሁን አንዱአለም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review