የኢትዮጵያ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየሰፋ መምጣቱን የስራና ክህሎት ሚንስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
የኢፌድሪ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 480 ሰልጣኞችን አስመርቋል::
በምረቃ ስነ ስርዓቱ የስራና ክህሎት ሚንስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ መንግስት ባለፉት ሰባት ዓመታት ለሆቴል ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘርፉን ለማሳደግ በጥናትና ምርምር የተደገፉ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን እንዳከናወነም ተናግረዋል፡፡
ተመራቂዎች የተሰጣቸው ሙያዊ ኃላፊነት ተምሮ ሰልጥኖ ስራ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገርን ማስተዋወቅ በመሆኑ ይህን ሀገራዊ ሀላፊነት በብቃት በመወጣት ለሀገራችሁ አምባሳደር እንድትሆኑ ሲሉ ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡
የኢፌድሪ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ፣ በመዲናችን አዲስ አበባም ሆነ እንደሀገር የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና መሰረተ ልማቶች የተስፋፉበት ጊዜ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋማችን፣ ትኩረቱን በሆቴልና ቱሪዝም ሙያዎች ላይ አድርጎ የንድፈ ሃሳብ እና ተግባር ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል::
ተመራቂዎችም በሰለጠኑበት ሙያ እራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ለማገልገል ከውጭ ለሚመጡ ቱሪስቶችም በአግባቡ ሀገራቸውን ለማስተዋወቅ ቃል ገብተዋል፡፡
በታምሩ ደምሴ