ኢራን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንግደም የፊታችን ዓርብ በኒውክሌር ጉዳይ በኢስታንቡል ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ሦስቱ የአውሮፓ ሀገራት ተቋርጦ የቆየው ድርድር የማይቀጥል ከሆነ በቴህራን ላይ ዳግም ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ወደ መጣል እንደሚያመሩ አስጠንቅቀው ነበር።
ድርድሩ ለዓርብ የተቀጠረው፣ ሐሙስ ዕለት የሦስቱ የአውሮፓ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ፣ ከአንድ ወር በፊት በእስራኤል እና በአሜሪካ የኒውክሌር ጣቢያዎቿ ከተመቱባት ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከመከሩ በኋላ መሆኑም ተገልጿል።
በሀገራቱ መካከል የሚካሄደው ስብሰባም በምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረግ መሆኑን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጌ መናገራቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በፈረንጆቹ 2015 ከኢራን ጋር በተደረገው የኒውክሌር ስምምነት ላይ የተሳተፉት ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩስያ እና አሜሪካ ነበሩ።
በታምራት ቢሻው