የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሠላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ መግባታቸው ተገልጿል።
የፊታችን ሀምሌ 19 ቀን የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር ለማስቻል እየተከናወኑ ባሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ዙሪያ ጥምር የፀጥታ አካላት በድሬዳዋ ከተማ ውይይት ማድረጋቸዉ ተገልጿል።
ጥምር የፀጥታ አካላቱ ከበዓለ ንግሱ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የወንጀል ተግባራትን አስቀድሞ ለመከላከልና የበዓሉ ታዳሚዎች ወደ ቦታው ሲሄዱና በዓሉን አክብረው ሲመለሱ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው ከፍተኛ ዝግጅት አድርገው ወደ ስራ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።
በተለይም ከጥበቃና ከፀጥታ ማስከበር ሥራ ባሻገር የትራፊክ እንቅስቃሴው የተሳለጠ እንዲሆን የበዓሉ ታዳሚዎችን ያማከለ የትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱም ተመላክቷል።