መንግሥት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 32 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ

You are currently viewing መንግሥት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 32 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ

AMN ሐምሌ 15/2017

መንግስት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከሁሉም ምንጮች 32 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

የግሉ ዘርፍ ተዋናዮችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና የፋይናንስ ተቋማትን በማሳተፍ በዘላቂ ልማት፣ በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊና በንግድ ዙሪያ የሚመክረው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባኤ የግል ዘርፍ መድረክ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በዚህ ወቅት፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እና ቀጣይነት ያለው የሀገር ዕድገትን ለማረጋገጥ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ገቢራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም የዋጋ ግሽበትን በግማሽ መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን በማድረግ የምንዛሬ ክምችትን ማሳደግ እንዲሁም በመሰረታዊ ዘርፎች ላይ ምርታማነትን መጨመር ተችሏል ብለዋል።

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውም አስደናቂ ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው፥ ዘመናዊና ለልማት የሚመች የፋይናንስ ዘርፍ እንዲኖር ምቹ ሀኔታ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት በ2016 በጀት ዓመት ከሁሉም ምንጮች ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት 24 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታወሰው፣ ከተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወዲህ በ2017 በጀት ዓመት 32 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን መግለቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሀገር እድገት በመንግስት ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም ያሉት የባንኩ ገዥ፤ የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የዛሬው ጉባኤም የግሉ ዘርፍ በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ ግልጽነት በመፍጠር በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል ምክክር የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትብብር ባዘጋጁት ጉባኤ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የባንክ ፕሬዝዳንቶችና የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ታድመዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርምና የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ ለአካታች ፋይናንስና ልማት የብድር አገልግሎት ማመቻቸት፣ የኢንቨስትመንት ከባቢ በኢትዮጵያ እና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በመርሀ ግብሩ የፓናል ውይይት የሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review