የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን ኢትዮጵያ ታላላቅ የአትሌቲክስ ውድድሮችን የማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላት ተናግሯል፡፡
በአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድር ላይ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ የእውቅና እና ሽልማት መርሃ-ግብር በተካሄደበት ወቅት መልዕክት ያስተላለፈው ፕሬዝዳንቱ
’’ኬንያ የ2029 ወይም 2031 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት አሳውቃለች ፤ እኛም በዚህ ደረጃ መፎካከር እንፈልጋለን ፤ አሁን ጥሩ ተስፋዎች አሉ ፤ አደይ አበባ ስታዲየም በጥሩ መንገድ እየተሰራ እንደሆነ እናውቃለን ፤ በተያዘለት ጊዜ ከተጠናቀቀ ትልልቅ ውድድሮችን ማዘጋጀት እንችላለን ፡፡’’ ሲል ተናግሯል፡፡
የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ ንግግር መጀመሩንም ኮማንደር ስለሺ አያይዞ ጠቁሟል፡፡ ’’አሁን ላይ ተስፋ እያየን ነው፡፡ የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራዎች በፍጥነት እንደሚጠናቀቁ በማመን ለአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ውድድር እንድናዘጋጅ የሚያስችል ጥያቄ አቅርበናል፡፡’’ በማለት ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻፒዮናን 2000 ዓ.ም ላይ ማዘጋጀቷ ይታወሳል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ በአፍሪካ ተከናውኖ አያውቅም፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ