የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ በቢሾፍቱ እየተካሄደ ይገኛል።
የሰላም ሚኒስቴር በሀገር ደረጃ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ሰላምን ለማስፈን እና ለማስጠበቅ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ተናግረዋል።
በሀገራችን ሰላምን በማስፈን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጎልበት፣ የሀገረ መንግስት ግንባታውን በማጠናከር ሂደት ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት እንዲሁም ህግን በማስከበር ረገድ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በዚህም በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል አንፃራዊ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
ሰላምን በማፅናት ረገድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ቀድሞ ከመንግስት ጎን በመቆም ሚናቸውን ሊጫወቱ እንደሚገባም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ሀይሌ በበኩላቸው፣ ምክር ቤቱ ሀገራዊ ሰላምን ማስፈንና ማፅናትን ዓላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ሰብሳቢው አክለውም ይህ የሰላም ኮንፍረንስ በዋናነት በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩ ግጭቶችን በሰላም እንዲፈቱና ሀገራዊ ምክክሩ ፍሬ እንዲያፈራ እንዲሁም ቀጣዩ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በራሄል አበበ