የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ የ2017 አፈጻጸምን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት አመት 162 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታዉቀዋል፡፡ ገቢው የእቅዱ 99 በመቶ መሆኑን ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል ።
የገቢ ምንጮችን በማስፋት በበጀት አመቱ ከፋተኛ ገቢ ማግኘቱን የተናገሩት ስራ አስፈጻሚዋ ገቢው ካለፈው አመት ጋር የ72.8 በመቶ እድገት አሳይቷል ብለዋል።
ገቢውም ከድምጽ ከኢንተርኔትና ከውጪ ጥሪዎች እና ሌሎች የገቢ አማራጮች የተገኘ መሆኑን የገለጽጹት ፍሬህይወት ታምሩ 28.6 በመቶው ከድምጽ 22.3 በመቶ ደግሞ ከኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የተገኘ ነው ብለዋል።
የኔትዎርክ ማስፋፋት የደንበኞች ቁጥር መጨመር እና ተመጣጣኝ አገልግሎት የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለእድገቱ ቁልፍ ሚና መጫወታቸውም ተመላክቷል።
በበጀት አመቱም የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር 83.2 ሚሊየን ደርሷል ነው የተባለው።
4 አመታትን ያስቆጠረውና የፋይናንስ አገልግሎትን ያነቃቃው የቴሌ ብር ደንበኞች ቁጥርም 54.8 ሚሊየን መድረሱን ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
4.9 ትሪሊየን ብር ማንቀሳቀስ መቻሉም ነው የተገለጸው።
በበጀት አመቱም 7 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞች በመቀላቀል 2.3 ትሪሊዮን ብር ማንቀሳቀስ ተችሏል ተብሏል።
የቴሌ ብር አገልግሎት ከ29 ባንኮች እና 369ተቋማት ጋር ተሳስሮ እየሰራ እንደሚገኝም ነው ፍሬህይወት የተናገሩት።
በቴሌብር አማካኝነት ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች 12.3 ቢሊየን ብር ብድር መጠቀማቸውን የገለጸው ኩባንያው 1.7 ሚሊየን ደንበኞች ደግሞ 11 ቢሊየን ብር ቆጥበዋል ።
በፍቃዱ መለሰ