የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን የሚያበስር ሀገራዊ ስኬትና የከፍታ ጉዞ ማሳያ ተግባር መሆኑ ተገለጸ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና ሌሎች የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በጎንደር ከተማ በአንገረብ ተፋሰስ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራውን ዛሬ አኑሯል።
ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ትውልድ ተሻጋሪና በሕዝቦች መካከልም በጋራ የመስራት ባህልን እያዳበረ የመጣ አኩሪ ተግባር ነው።
እንደ ሀገር በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ እንደሚተከል አውስተዋል።
ሚኒስትሩ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን የሚያበስር ሀገራዊ ስኬትና የከፍታ ጉዞ ማሳያ ተግባር ነው ብለዋል።
ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦና አጽድቆ ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ሕዝቡም ለተግባራዊነቱ እንዲረባረብ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጎንደር ከተማ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሀገር በቀልና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያለው ችግኝ እየተተከለ መሆኑን የገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው።
በአንገረብ ተፋሰስ ዛሬ የተከናወነው የችግኝ ተከላ ለከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ የሚያቀርብውን የአንገረብ መጠጥ ውሃ ግድብ ከደለል በመከላከል የሚሰጠውን አገልግሎቱ ለማራዘም የላቀ ጠቀሜታ አለው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢንዱስትሪ እና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በቆይታቸው በከተማው የአቅመ ደካማ ወገኖች መኖሪያ ቤት እድሳት ስራ የሚያስጀምሩ ሲሆን፤ ለችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደርጉም ታውቋል።
በሥነ-ሥርዓቱ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።