የኩላሊት ህመም የበርካቶችን ቤት በማንኳኳት የብዙዎችን ሀብትና ንብረት እያሟጠጠ ይገኛል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ህክምናዉን ማግኘት እየፈለጉ እጅ አጥሮአቸዉ የሚሰቃዩ ዜጎች ቁጥርም ጥቂት የሚባል አይደልም፡፡
ለዜጎች የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ መፈጠር ህመሙን ያከብደዋል።
የኩላሊት እጥበት ማሽኖች ድጋፍ የህሙማንን የመኖር ተስፋ ያለመለመ መሆኑን ታዳጊ ቤተልሔም መኮንን ገለጸች፡፡
ቤተልሄም አንድ ቀን በተሰማት ህመም ሳቢያ ወደ አቅራቢያዋ ጤና ጣቢያ ብታመራም ለተጨማሪ ምርመራ በሪፈር ወደ ጥቁር አንበሳ ከሄደች በኋለ ነበር የኩላሊት ታማሚ መሆኗን የተረዳችው።
ባለ ታሪኳ ታዳጊ ቤተልሄም መኮንን ህመሙ ከአራት አመት በፊት ገና በ13 አመቷ አንደጀመራት ለኤ ኤም ኤን ትናገራለች።
የህመሙን ችግር እና አስከፊነት ገና በለጋ ዕድሜዋ የተረዳችው ቤተልሔም ለህክምናው ወጪ ቤተሰቦቿ ያላችውን ጥሪት አሟጠው የሠው ፊት ሲገርፋቸው ማየት ከህመሙ በላይ ሌላ ህመም ነበር ትላለች።
ለአንድ ጊዜ ዲያሊስስ የሚከፈለው ክፍያ ወጪ መብዛት ተምራ ፓይለት የመሆን ተስፋዋን እንዳጨለመባትም በትካዜ ትናገራለች።
ቀናት ቀናትን እየወለዱ በሄዱ ቁጥርም የታዳጊ ቤተልሔምና ሌሎች ዜጎች ተስፋ የሚያለመልም የብስራት ዜና ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተሰማ።
ተቋሙ ለዳግማዊ ሚኒሊክ ኮምፕሪኤሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 20 የኩላሊት እጥበት ማሽኖችን ጨምሮ ለ180 ህሙማን የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ለግሷል።
የሠው ፊት ከማየት ብሎም ከስነ ልቦና ጫና በመላቀቅ የመኖር ተስፋዋን እንዳለመለመላትና ለተደረገላትም አበርክቶ ምስጋናዋ ከፍ ያለና እፎይታን የሰጠ መሆኑን ታዳጊ ቤተልሔም ትናገራለች።
የመኖር ተስፋዋ የጨመረው ታዳጊዋ ለተደረገላት አበርክቶና የህክምና ባለሙያዎች መታሰቢያም ተምራ ህክምና ማጥናት ህልሟ መሆኑን አብራርታለች።
ሌሎች ታካሚዎችም የኩላሊት እጥበት ማሽኖቹ የመኖር ተስፋቸዉን እንዳለመለሙላቸው ነዉ ያረጋገጡት፡፡
ድጋፉ ህይወት የማስቀጠል ታሪካዊ ሃላፈነትንም የመወጣት እንደሆነ የሆስፒታሉ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተከተል ጥላሁን ገልፀዋል።
በሚካኤል ህሩይ