አዲስ አበባ በብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የከተሞች ውድድር ከመጨረሻዎቹ 50 ዕጩዎች መካከል አንዷ ሆነች

You are currently viewing አዲስ አበባ በብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የከተሞች ውድድር ከመጨረሻዎቹ 50 ዕጩዎች መካከል አንዷ ሆነች

AMN-ሐምሌ 2017 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከተማ በብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የከተሞች ውድድር (Mayor’s Challenge) 2025 ከመጨረሻዎቹ 50 ዕጩዎች መካከል አንዷ ሆናለች።

መዲናዋ ይህንን ደረጃ ያገኘችው በአለም አቀፍ ደረጃ በመርሃ ግብሩ ለመወዳደር ካመለከቱ 630 ከተሞች መካከል ተመርጣ ነው።

በብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ አማካኝነት የሚዘጋጀው ይህ ውድድር ከተሞች ለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች የሚወስዱትን ችግር ፈቺ የመፍትሄ ርምጃ ፤ በመረጃ ላይ የተመሰረተ እና ሊሰፋ የሚችል መሆኑን መለየት እና መደገፍን ያለመ ነው።

የዘንድሮው ውድድርም የከተሞችን ፈርጀ ብዙ ችግሮችን በአዲስ የፈጠራ ሃሳብ በመፍታት ሰው ተኮር የሆነ የከተማ ትራንስፎርሜሽንን ማምጣት መቻል ላይ ያተኮረ ነው።

በዚህም አዲስ አበባ ዘመናዊ፣ የተቀናጀ እና በአንድ ማዕከል የተደራጀ የመረጃ ስርዓትን በመጠቀም የነዋሪዎቿን ችግሮች ለመፍታት ባቀረበችው የመወዳደሪያ ዝክረ ሃሳብ ተመርጣለች።

የአዲስ አበባ ከተማ የፈጠራ ልዑክ ቡድንም በቦጎታ ኮሎምቢያ እየተካሄደ ባለው የብሉምበርግ የውድድር ሃሳቦች ካምፕ ተገኝቷል።

በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የብሉምበርግ የከንቲባዎች ውድድር ከሁሉም አህጉራት ካሉ ከተሞች ተሳትፎን የሚስብ ትልቅ ዓለም አቀፍ ውድድር ሲሆን በዚህ ዓመትም ከምርጥ 50 ከተሞች መካከል ቶሮንቶ፣ ሴኡል፣ ኬፕ ታውን፣ ሲያትል፣ ሳን ፍራንሲስኮ፣ ቫንኮቨር፣ ቡዳፔስት፣ ማርሴይ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ እና ሌሎችም ከተለያዩ አህጉራት እንደሚገኙበት የብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ መረጃ ያመለክታል።

እነዚህ 50ዎቹ የመጨረሻ እጩዎች አለም አቀፍ በሆኑ ባለሙያዎች የቴክኒክ ድገፍ እየተደረገላቸው ቆይተው የመወዳደሪያ ሃሳቦቻቸውን ያዳብራሉ።

በመጨረሻም የሚመረጡት 25 ተወዳዳሪዎች ችግር ፈቺ የሆኑ ሃሳበቻቸውን ለመተግበር የሚያግዝ ለእያንዳንዳቸው የአንድ ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ ይሆናል።

አዲስ አበባ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሽልማቶችን ማግኘቷ ይታወቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review