በተቀመጠው አዋጅ መሠረት በከተማዋ የሚገኙ ነጋዴዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ክፍያን መክፈል እንደሚኖርባቸው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ በ2017 የበጀት ዓመትና የተከናወኑ አበይት ተግባራትን በተመለከተ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ማቀፍ ሲቻል አንድ ነጥ ሶስት ሚሊየን የሚሆኑት አገልግሎቱን ማግኘት እንደቻሉም አብራርተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ለጤና መድህኑ ድጎማ ያደረገ ሲሆን ይህም የነዋሪዎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ህብረተሰቡ ወደ ጤና ተቋም መምጣትን ባህል እንዲያደርግ እገዛ አርጓልም ብለዋል።
አንድ ሰው በኪሱ ገንዘብ ሳይኖረው የህክምና አገልግሎት ማግኘት መቻሉ፣የህክምና ወጪ ለመቀነስ ማገዙ፣በህብረተሰቡ ዘንድም መደጋገፍን ለማጎልበት ማስቻሉ ጠቀሜታውን የጎላ ያደርገዋል ያሉት ዶ/ር ዮሐንስ በአዲሱ በጀት ዓመትም ስራው በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
በተለይም በአዋጅ ቁጥር 1273/74 ድንጋጌ መሠረት መካተት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በማካተት ክፍያውን እንዲፈፅሙ ማስቻል ትኩረት ተሰጥቶታል።
አዋጁ ቋሚ ገቢ የሌላቸውና ግብር ከፋይ ነጋዴዎች የጤና መድህኑን ክፍያ መክፈል አንዳለባቸው ቢደነግግም የመክፈል የሚገባቸውን መጠን ለመወሰን በቂ ጥናትና አሰራር ማመቻቸት ሲደረግ መቆየቱን ኃላፊው አክለዋል።
በዚህም መሠረት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው በነባሩ ክፍያ ሲቀጥሉ፣ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በየደረጃቸው መሠረት ከገቢ መጠናቸው መክፈል የሚኖርባቸው ክፍያ ጥናት በመጠናቀቁ የደረጃ ሀ 10 ሺህ 500 ብር፣ደረጃ ለ 6 ሺህ 900 ብር እና የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮችም 2 ሺህ ብር እንደ ገቢ መጠናቸው እንዲከፍሉ አዋጁ ያስገድዳል ብለዋል።
በመሆኑም የከተማዋ የንግዱ ማህበረሰብ የጤና መድህን ሽፋኑ ተጠቃሚ ብሎም የመረዳዳትና መደጋገፍ ባህሉን መሠረት ታሳቢ በማድረግ ክፍያውን እንዲከፍልና ቢሮውም አዋጁን የማስፈፀም ተግባሩን በትኩረት እንደሚሠራ አሳስበዋል።
የነጋዴው ማህበረሰብ የጤና መድህን ሽፋን ክፍያ እንጂ ተጨማሪ እዳ አለመሆኑን በመገንዘብ በግብር መክፈያ ጣቢያቸው በተቀመጠ አካውንት በቴሌ ብርና በንግድ ባንክ ገቢ በማድረግ ሚናውን እንዲወጣ አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።
ሚካኤል ህሩይ