ከበሽር አል አሳድ ውድቀት በኃላ ሳዑዲ አረቢያ ለአዲሱ የሶሪያ መንግስት ዋና ደጋፊ ሀገር መሆኗ ይነገራል፡፡
ለ14 ዓመታት ያህል የእርስ በርስ ጦርነት ያወደማትን ሀገር ፤ ሳዑዲ አረቢያ በሪል እስቴት እና በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሃብት ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት አስታውቃለች።
የሳዑዲ አረቢያ የኢንቨስትመንት ሚኒስትር የሆኑት ፤ ካሊድ አል-ፋሊህ ሃሙስ በደማስቆ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የ6.4 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል ።
በአል ፋሊህ የሚመራው የልኡካን ቡድን 150 የሚሆኑ ባለሃብቶችን ፣ የሳዑዲ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮችን ያካተተ ሲሆን ፤ ዕሮብ እለት በዋና ከተማዋ ውስጥ ከሚካሄደው የቢዝነስ ፎረም በፊት በተደረገው ስብሰባ ላይ መሳተፋቸውን አልጀዚራ ዘግባል።
ማክሰኞ እለት የሳዑዲ የኢንቨስትመንት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ፤ የደማስቆ ፎረም የትብብር እድሎችን ለመፈተሽ እና ዘላቂ ልማትን የሚያጎለብቱ እና የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ስምምነቶችን ለመፈራረም ያለመ ነው ብሏል።
ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታር በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ፤ የሶሪያን እዳ ለአለም ባንክ በድምሩ ወደ 15 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ቃል መግባታቸው ተገልጿል ።
ባለፈው ሳምንት እስራኤል በደማስቆ መሀል ከተማ ላይ በርካታ የአየር ድብደባ ማድረጓ ታውቋል።
በዋና ከተማው ላይ የተፈፀመው ጥቃት በሱዋይዳ በተፈጠረው አለመረጋጋት በመሆኑ ፤ የአካባቢው የቤዱዊን ጎሳዎች ከድሩዝ አናሳ ጎሳዎች ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
በአሜሪካ አሸማጋይነት የእስራኤል እና የሶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት የተነሳ ፤ አልሻራ በደቡባዊ ሶሪያ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ማውጣቱን አስታውቋል፣ ይህም ለበርካታ ቀናት መቆየቱ ታውቋል።
የሶሪያ መንግስት በሱዋይዳ ውስጥ የታሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤዱዊን ቤተሰቦችን ማስለቀቁን አልጀዚራ ዘግቧል።
በብርሃኑ ወርቅነህ