ፈረንሳይ በመስከረም ወር ለፍልስጤም መንግስት ይፋዊ እውቅና እንደምትሰጥ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስታውቀዋል።
ይህን በማድረጓም ፈረንሳይን የመጀመሪያዋ የቡድን 7 ሀገር ያደርጋታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ማክሮን ይህንን ውሳኔ በኒው ዮርክ በሚካሄደው በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደሚያሳውቁ በኤክስ ገፃቸው አስፍረዋል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት የማክሮንን ውሳኔ የተቀበሉ ሲሆን፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው የፈረንሳይን ውሳኔ ውድቅ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው፣ የማክሮንን ውሳኔ “ግዴለሽነት የታየበት” ሲሉ ተናግረዋል ።
አሁን ላይ የፍልስጤም ግዛት ከ193 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት ወስጥ፣ ከ140 ሀገራት በላይ እውቅና መስጠታቸው የታወቀ ሲሆን፣ ስፔንና አየርላንድን ጨምሮ ጥቂት የአውሮፓ ህብረት ሀገራትም እንደሚገኙበት ተዘግቧል።
ነገር ግን እንግሊዝን ጨምሮ የእስራኤል ዋና ደጋፊ የሆነችው አሜሪካ እና አጋሮቿ ለፍልስጤም መንግስት እውቅና አለመስጠታቸው ተመላክቷል።
የሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፈረንሳይን ውሳኔ አድንቆ፣ የፍልስጤም ህዝቦች የራስን በራስ የመወሰን መብት እና ነፃ ሀገር መመስረት ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን ያረጋግጣል ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋዛ ሰርጥ ብዙዎች ለረሃብ እንደሚጋለጡ በማስጠንቀቅ፣ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጠቁመዋል።
በብርሃኑ ወርቅነህ