የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአንድ ጀምበር ሚሊየኖችን በመትከል የማንሰራራት ታሪካዊ ጉዞ አካል እንሁን በማለት መግለጫ አዉጥቷል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣዉ መግለጫዉ እንደሚከተለዉ ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ነበራት ጥንታዊ የደን ሽፋን በመመለስ አረንጓዴ ካባ ለማልበስ የጀመርነው ጥረት 7ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል፤ 7ኛ ዓመት የጥረታችንን ጅማሮ የምንዘክረዉ ደግሞ በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ነው፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዟችን ኢትዮጵያውያን ከሁሉም አቅጣጫ፣ ከደጋ እስከ ቆላ በጋራ ባደረግነዉ ጥረት 40 ቢሊዮን ችግኞች በላይ ተክለናል፤ የኢትዮጵያን የደን ሽፋንም እስከ ባለፈዉ ዓመት ድረስ ወደ 23% ማሳደግ ችለናል፡፡ በአንድ ጀምበር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር እና በአጠቃላይ በክረምቱ 7.5 ቢሊዮን ችግኞችን የተከልንበት የባለፈዉ ክረምት የጽድቀት መጠን ሲጨመርበት የደን ሽፋናችን ከዚህም ይልቃል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ የሚተከሉት ሀገር በቀል የደን እና የውበት ዛፎች ብቻም አይደሉም፤ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የፍራፍሬ በስፋት በመተከል ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄያችን በተተከሉ ችግኞች የፍራፍሬ ፍላጎታችንን ለማሟላት ብዙ ርቀት ሄደናል፤ እንደ አቮካዶ ያሉ በዓለም ገበያ ተፈላጊ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክም ጀምረናል፡፡
አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ከመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥም ባሻገር ኢትዮጵያውያን በጋራ ጥረታችን እና በላባችን በፈጠርነዉ ጥሪታችን የገነባናቸዉ ግድቦቻችንን ከደለል ለመታደግ የሚያስችለን ጭምር ነው፡፡ ዐሻራችን ያኖርንባቸዉ ግድቦቻችንን በአረንጓዴ ዐሻራችን በማፅናት ዳግም ታሪክ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
ዘንድሮም እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የራሳችንን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ክብረ ወሰን ለማሻሻል ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘናል፡፡ መላው ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከደጋ እስከ ቆላ ተነቃንቀን በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን እንተክላለን፤ በመትከል እናንሰራራለን፡፡ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የሚያለብሰው ትውልድ አካል ነንና ከታዳጊዎች እስከ አረጋውያን፣ ከመንግሥት ሠራተኛ እስከ ግል ተቋማትና ግለሰቦች ኹላችንም አረንጓዴ ዐሻራችንን እናኖራለን፡፡
በተያዘዉ ክረምት የምንተክለው 7.5 ቢሊዮን ችግኝ በሰባት ዓመታት የተከልነዉን አጠቃላይ የችግኝ መጠን ወደ 48 ቢሊዮን የሚያስጠጋ ነው፡፡ ለዚህ ክረምቱ መርሐ ግብር በአጠቃላይ ከ8.5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል፡፡ እየተከልናቸው ያሉ ችግኞችም የደን፣ የፍራፍሬ፣ የውበት በመኾናቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከማስቻል ባሻገር ለምግብ ሉዓላዊነታችን መረጋገጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በጋራ ለጋራ ስኬት በመትከል ለማንሰራራት እየተጋን የምንገኘው፡፡
በክረምቱ መውጫ ኢትዮጵያ የምታስተናግደዉን 2ኛዉ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤም የአረንጓዴ ዐሻራ ልምዷን ለሌሎች የምታካፍልበት ዕድል አድርጋ ትወስደዋለች፡፡ በዚህም አረንጓዴ ዐሻራችንን በማኖር ዳግም ታሪክ እንድንሠራ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በመትከል እናንሰራራለን!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት