ሀሳብ ከተማን ያንፃል፤ የታነጸ ከተማ፣ የተዋበ መዲና ደግሞ ለጥበብ በር ይከፍታል።
ማራኪ ከባቢ ጠቢባንን ከሩቅ ጠርቶ ከያኒው፣ ጸሐፊው፣ ሰዓሊው፣ ሙዚቀኛው በአጠቃላይ ሁሉም የኪነ ጥበብ ባለሙያ በብዕሩ፣ በብሩሹ፣ በአንደበቱ ሃሳብን እንዲያፈልቅ ያነቃቃል።
አመሰራረቷ እና ስያሜዋ ከውበት ጋር አጅግ የተሳሰረችው አዲስ አበባም ከኪነ-ጥበብ ጋር ረዘም ያለ ግንኙነት አላት።
አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ ከማዕከላዊ መናገሻነት ባሻገር የጥበብ ማዕከልም ሆና አገልግላለች፤ እያገለገልችም ትገኛለች።
ዘመናትን የተሻገሩት ቴአትር ቤቶችና የኪነ-ጥበብ ማዕከላትም ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው።
ነገር ግን አዲስ አበባ ያላትን አስደናቂ የተፈጥሮ፣ የታሪክና የማህበረሰብ አወቃቀር በሚመጥን ልክ የኪነ-ጥበብ ዘርፉ እንዳላደገ በርካቶች ይስማማሉ።
ለበርካታ ዘመናት ከከተማዋ እድገት ጋር የሚጣጣም የኪነ-ጥበብ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ስራ በሚፈለገው ልክ አለመከናወኑ ደግሞ ለዚህ በምክንያትነት ሲነሳ ቆይቷል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አዲስ አበባን እንደ ስሟ “አዲስ” እና “አበባ” ማድረግ በሚል እሳቤ ከተማዋን ለመለወጥ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ለኪነ-ጥበብ ዘርፍ ልዩ ትኩረት የሰጡ ሆነዋል።
በገበታ ለሸገር መርሐ-ግብር የተከናወኑ የልማት ስራዎች በርካታ አምፊ ቴአትሮች፣ ሰፊ ህዝብን መያዝ የሚችሉ ፓርኮች እንዲሁም የአርት ጋላሪ ጭምር ያካተቱ መሆናቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
የኮሪደር ልማቱ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ ይህ ተግባር ይበልጥ ሰፍቶ ዛሬ ላይ በተለያዩ የአዲስ አበባ አከባቢዎች አምፊ ቴአትሮችን ጨምሮ ህዝብ ሰብሰብ ብሎ የተለያዩ ሁነቶችን የሚከውኑባቸው ስፍራዎችን ማግኘት ብርቅ አይደለም።
በመዲናዋ የስዕል አውደ ርዕይ ስራዎቹን እያሳየ የሚገኘው ሰዓሊ የአዲስ አበባ የመሰረተ ልማት መስፋፋት ስራዎች ለኪነ-ጥበብ ትኩረት የሰጡ መሆናቸው ዘርፉን ለማሳደግ ትልቅ እድል ስለመሆኑ ይናገራል።
“አንድ እጅ አጨብጭቦ አንድ በሬ ስቦ” እንዲሉ ዘርፉ ይበልጥ እንዲያድግ መንግስት ከሰጠው ትኩረት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍም በኪነ-ጥበብ መሰረተ ልማት ላይ መሳታፍ እንዳለበት ሰዓሊ ኪሩቤል መልኬ ይናገራል።
በተለይ በመዲናዋ ግዙፍ ህንጻ የሚገነቡ ባለሃብቶች በግንባታቸው ውስጥ አርት ጋለሪና ለኪነ-ጥበብ ማከናወኛ ስፍራ በማካተት በትውልድ ግንባታ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ እንዳለባቸውም ያነሳል።
ኪነ ጥበብ ማህበረሰብን በማቀራረብ ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሷል።
ቸርችል አካባቢ መልከ ሀሳብ የተሰኘውን አውደ ርዕይ በወረቀት፣ በጨርቃ ጨርቅ እና በባይንደሮች በመጠቀም በርከት ያሉ ስራዎችን አቅርቧል።
”መልከ ሀሳብ” የሚለውን ስያሜ በኤግዚቢሽኑ አጋፋሪ (curator) ሜሪ ሸዊት ዦን አማካኝነት የተሰየመ ሲሆን፣ ስዕሎቹ የተሰሩበትን ቁስ ለመግለፅ በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ አውደ ርዕይ በትንንሽ መጠን 12 ስራዎች፣ በትልልቅ መጠን ደግሞ ወደ አስራ አራት ስራዎች ለእይታ ቀርበዋል።
ሰዓሊው አንድ ከሀገር ውጭ እና አምስት ጊዜ ደግሞ በሀገር ውስጥ ማቅረቡን ገልፆ፤ የቡድን የስዕል አውደርዕይ በተለያየ ጊዜ አቅርቧል።
የስዕሎቹ ሀሳብ
በስዕሎቹ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን ለማንፀባረቅ መሞከሩን ያስረዳው ሰዓሊ ኪሩቤል፣ የተለያዩ ቁሶችን ሰብስቦ በመሰራቱ ቁሱ በራሱ የሚፈጥረው ሀሳብ መኖሩን ይገልፃል።
በልብስ ቁርጥራጭ የሰራውን ስዕል በምሳሌነት ያነሳ ሲሆን፣ የምንለብሳቸው ልብሶች ብርድን ከመከላከል በተጨማሪ ሀሳብን ነው የሚናገሩት በማለት ያብራራል።
ለዚህም ምሳሌ ህንፃ የሚገነቡ ግለሰቦችን ያነሳው ሰዓሊው፣ በራስ አቅምና ጉልበት የተሰራን ህንፃ በሌላ ሀገር ስያሜ ሲሰጣቸው ይስተዋላል።
ስም ስያሜ ብቻ አይደለም የሚለው ሰዓሊው፣ ስንሰይም በስም ውስጥ ያለውን ፍልስፍና ለትውልድ የምንነግረውን ታሪክ ታሳቢ ያደረገ ነው ብሏል።
በአጠቃላይ በስዕሉ ለመንገር የፈለገው ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ፣ በሀገር በግለሰብ ደረጃ ያለውን የሚተርክ የሥዕል ሥራም መሆኑን፣ በሚያደርጉልን ልክ መጠፍነግ የሚፈልጉ መኖራቸውን የሚጠቁም ነው ብሏል፡፡
በመጨረሻም በአዲስ አበባ የተለያዩ የስዕል ኤግዚቢሽን ማሳያዎች ቢኖሩም፣ ካለው የሰዓሊ ብዛትና የሕዝብ ብዛት አኳያ አሁንም ተጨማሪ ቦታዎች ያስፈልጋል ብሏል።
በብሉ ስቱዲዮ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ለህዝብ ክፍት የሆነው የስዕል አውደ ርዕይ እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል።
በሔለን ተስፋዬ