የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በአንድ ማዕከል ማድረግ ቴክኖሎጂንና የሰው ኃይልን በአግባቡ ለመጠቀም እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበሩ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉ የመንግስት አገልግሎት ተቋማትን በጥናትና ምርምር በመታገዝ፤ ተቀራራቢ አገልግሎት አሰጣጥን እንዲሁም ቴክኖሎጂን ታሳቢ ባደረገ መንገድ በማደራጀት ፈጣንና ቀልጣፋ ችግር ፈች አገልግሎት ለመስጠት ቅደመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱን ዶክተር ጀማሉ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አገልጋይ ፕሮግራም በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በአንድ ማዕከል በተደራጁ ተቋማት መደብ ያላገኙ ሰራተኞች ባላቸው የትምህርት ዝግጅት፣ የስራ ልምድና የሙያ ብቃት በሌሎች ክፍት ቦታዎች በመመደብ፣ ሰራተኛውን እያበቃን፣ ክፍተቶች ካሉ እያስተካከልን ለህብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት ለመስጠት እንሰራለን ብለዋል።
የሰራተኞች ጥቅማጥቅምን በተመለከተ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ያነሱት ኃላፊው፣ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በቴክኖሎጂ እቤቱ ሆኖ በመገልገል በአንድ ማዕከል የተጠቃለሉ በየደረጃው የነበሩ ተቋማት ማግኘት እንደሚችል አጽንኦት ሰጥተዋል።
የስራ ድግግሞሽን በመቀነስ፣ ወጭን በመቆጠብ የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ተቋም ለመፍጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተከናወነ ተቋማዊ አሰራር ተዘርግቷልም ብለዋል።
በአዲሱ ተቋማዊ አወቃቀር፣ የሰራተኛ ቅሬታ ካለ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
በአለኸኝ አዘነ