የተቋማት ማትጊያ ስንቅ

You are currently viewing የተቋማት ማትጊያ ስንቅ

. ሽልማቱ በቀጣይ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ አደራ መሆኑ ተገለፀ

በየትኛውም የስራ ዘርፍ ስኬትን ለማስመዝገብ፣ የሠራተኞች ተነሳሽነትና የተቋማት ውጤታማነት ወሳኝ ናቸው። ሠራተኞችን በብቃታቸው ማበረታታትና የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ተቋማትን መሸለም፣ ከወትሮው የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከሚያስችሉ ስልቶች ቀዳሚው ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተቋማትን
ሸልሟል፡፡ ይህም በአስተዳደሩ ውስጥ ውጤታማነትንና ተጠያቂነትን ለማጠናከር ወሳኝ ምዕራፍ ሲሆን፣ የተቋማትን የሥራ ተነሳሽነት ከመጨመር ባለፈ፣ ለሌሎችም የተሻለ ለመሥራት የሚያነሳሳ ተምሳሌት ተደርጎ ተወስዷል፡፡

የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ቢሮዎች፣ ተቋማት፣ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እውቅናና ሽልማት በተሰጠበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት የተገኘው ውጤት በየደረጃው ያለው የአስተዳደር አካል የጋራ ድምር ስኬት ነው ብለው፣ ሽልማቱ የሁሉም አመራር፣ በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች፣ የባለድርሻ አካላት እና ከአስተዳደሩ ጋር አብሮ ለሰራው ህዝብ የተሰጠ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በከተማ ደረጃ ሽልማት ከተበረከተላቸው ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒዩኬሽን ቢሮ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም በበጀት ዓመቱ ባስመዘገበው ስኬት ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እንደሚሰሩ በመግለጽ፣ ሚዲያዎቹ የተዛቡ መረጃዎችን በማረም እና የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን በተገቢው ወደ ህዝብ በማድረስ ለተወጡት ኃላፊነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡  በተለይም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በበጀት ዓመቱ የህዝቡን የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እንዲሁም ነዋሪውን ከአስተዳደሩ ጋር በማገናኘት ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህዝብና መንግስትን በማገናኘት የሚታወቅበት ‘ዋርካ’ እና ‘አገልጋይ’ ፕሮግራሞቹ የተሻለ ነጥብ እንዲያገኝ አስችሎታል ያሉት ከንቲባዋ፣ ‘አገልጋይ’ የተሰኘው እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በቀጥታ የስልክ መሥመር ከህዝብ ለሚነሳላቸው ጥየቄ ምላሽ የሚሰጡበት ነው፡፡ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በቀጥታ የስልክ መስመር የሚሳተፈውን ህዝብ ተሳትፎው የበለጠ መጨመር የሚያስችል ሥራ እንዲሰራም አሳስበዋል፡፡

‘ዋርካ’  የተሰኘው ሌላኛው ፕሮግራም እንደዚሁ ህዝቡ የመረጠውን የመንግስት አካል ፊት ለፊት በአካል የሚያገኝበት ዝግጅት ሲሆን፣ የተሰማውን ሀሳብና ጥያቄ በማቅረብ ከሚመራው አካል ጋር ወደ ተግባቦት የሚደረስበት እንደሆነም ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እስከታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ በመውረድ ሌት ተቀን ባከናወነው ተግባር ተመዝኖ ውጤታማ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ በኢንዱስትሪው የሚያደርገውን ግስጋሴ አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም አሳስበዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው የአፈፃፀም ሽልማት ለላቀ ስራ ማስፈንጠሪያ አቅም መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ ሽልማቱ የተሻለ ከፍ እንዲልና ሚዲያው ከነበረበት ሁለትና ሦስት እጥፍ እንዲሮጥ የሚያደርግ ማበረታቻ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተውበታል። ሽልማት በባህሪው ኃላፊነት መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ የሽልማት ማበረታቻው ተቋሙ የተሻለ እንዲሰራ አደራ ጭምር መሆኑን አመላክተዋል። አደራው በይዘት፣ በአቀራረብ፣ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል የተሻለ ሚዲያ እንዲሆን ማስቻልና መዲናዋን የሚመጥኑ መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ሀብተማርያም፣ ተቋሙ ለውጤት የበቃው ሰራተኛውና አመራሩ በጥሩ መንፈስ ተዋህደው በመስራታቸው ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡ አክለውም መሸለማቸው የቀጣይ ራዕያቸውን ከፍ እስኪል እንዲሰሩ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመው፣ ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው መስራታቸው ለውጤት እንዳበቃቸው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊድያ ግርማ በበኩላቸው፣ በፀጥታ ጉዳይ የውጤታማነት ትልቁ ምክንያት ከህዝብ ጋር መስራታችን ነው ይላሉ። የተሰጣቸው እውቅና ስራቸውን በላቀ ሁኔታ እንዲፈጽሙ ስንቅ እንደሚሆንላቸውም አመላክተዋል።

ታዲያ ይህ አይነቱ እውቅናና ሽልማት በሠራተኞች የሥራ መንፈስ፣ በተቋማት የዕድገት ሂደትና የአስተዳደሩን ግልጽነትና ቅልጥፍናን እንደዚሁም ለመልካም አስተዳደር እውን መሆን የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሚሆን እሙን ነው። የላቀ አፈጻጸም የሚያስገኙ ተቋማትን መመዘንና መሸለም ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደርና ትምህርት ክፍል አስጠንቶት በአሜሪካ ጆርናል ኦፍ ሎው እና ፐብሊክ አድምኒስትሬሽን ተቋም ላይ የታተመው ጥናታዊ ጽሑፍ ያስረዳል፡፡

ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ እንደተገለፀው ተቋማትን በአፈጻጸማቸው መሠረት መሸለም ለመልካም አስተዳደር እውን መሆን ወሳኝ ነው። ይህም ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ ከማበረታታቱም በላይ ሀብትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል። ሽልማት የሚከተሉትን የመልካም አስተዳደር መርሆዎች እንደሚያጠናክር የሚገልፁት ደግሞ የኤላ የማኔጅመንት ጉዳዮች አማካሪ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰላማዊት ግዛው ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በተለይ የአፈጻጸም ምዘናው ሂደት ግልጽ ሲሆን እና ሽልማቱ በግልጽ መስፈርት ላይ ሲመሠረት ተቋማት ለስራቸው ይበልጥ ተጠያቂ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ በህዝብ ዘንድ የመተማመን ስሜትን ይገነባል፡፡

አክለውም፣ እውቅና ተቋማት ሀብትን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጡ ያነሳሳል። የተሸለሙት ተቋማት በገንዘብ፣ በሰው ኃይል እና በጊዜ አጠቃቀም ረገድ የላቀ ብቃት አሳይተዋል ማለት ነው ይህ ደግሞ ለሌሎች ተቋማት መነሳሳትና በውድድር መስራት ወሳኝ ነው ሲሉ አስረድተዋል። ሠራተኞችና አመራሮች የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ያበረታታል። ሽልማቱ የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ ሰዎችና ተቋማት ዕውቅና ይሰጣል። ይህም የሥራ ሞራልን ከፍ በማድረግ ሁሉም ለበለጠ ውጤት እንዲተጉ ያደርጋል ሲሉ ወይዘሮ ሰላማዊት አብራርተዋል። ይህ ደግሞ ሠራተኞች የራሳቸው ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ይረዳል። የሽልማት ሂደቱ ህጋዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መካሄዱ፣ በአስተዳደሩ ላይ እምነት እንዲኖር ያግዛል፤ ተቋማት በብቃት፣ በሕግና በሥነ-ምግባር መርሆዎች መሠረት እንዲሠሩ ይበረታታሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሰላማዊት አፈጻጸምን መሠረት ያደረጉ ሽልማቶች የአንድ ጊዜ ተግባር ብቻ መሆን የለበትም ብለዋል። ሽልማቶቹ በመደበኛነት የሚሰጡ ከሆነ፣ ተቋማት ሁልጊዜም ቢሆን የተሻለ ለመሆን ይጥራሉ። በተጨማሪም ሽልማት የወሰዱ ተቋማት መልካም ልምዶቻቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ የሚያስችል መድረክ መፈጠር እንዳለበትም ጠቁመዋል። የላቀ አፈጻጸምን መሸለም የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ እርምጃ ነውም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ የከተማ አስተዳደሩ ለዜጎች የሚሰጠውን የአገልግሎት ጥራት ከማሳደግ ባለፈ፣ አስተዳደሩን ይበልጥ ውጤታማና ኃላፊነት የሚሰማው እንዲሆን ያደርጋል በማለትም አብራርተዋል።

ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) ፐርፎርማንስ ማኔጅመንት ኢን ዘ ሲቪል ስርቪስ (PERFORMANCE MANAGEMENT IN THE CIVIL SERVICE) በሚል ርዕሰ ባካሄዱት ጥናት በተቋማት መካከል ጤናማ ፉክክር እንዲፈጠር ምዘናና ሽልማት የግድ ነው ይላሉ፡፡ እያንዳንዱ ተቋም የተሻለ ለመሆን እና ሽልማቱን ለማግኘት መጣር ይጀምራል። ይህ ፉክክር በአጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት እንዲጠናከር ይረዳል፡፡ የሽልማት ሥርዓቱ የተቋማትን አፈጻጸም በግልጽ በመመዘን እና በማሳየት ተጠያቂነትን ያጠናክራል፡፡ ደካማ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋማት ለምን የተሻለ ውጤት እንዳላመጡ እንዲገመግሙና ክፍተቶቻቸውን እንዲያስተካክሉ ግፊት የሚያደርግ አሰራር ስለመሆኑም በጥናታዊ ፅሑፋቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

የሽልማትና እውቅና አሰራር የአንድ ጊዜ ክስተት ብቻ ሳይሆን፣ ተከታታይነት ያለው ሂደት መሆን እንዳለበት የገመቹ (ዶ/ር) ጥናታዊ ፅሑፍ ያብራራል። የሽልማት መስፈርቶችን ግልጽ እና ፍትሐዊ ማድረግ እንዲሁም የአፈጻጸም ምዘና ሥርዓቱን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርበታል፡፡ በተመሳሳይ፣ ሽልማት ከገንዘብ ነክ ጥቅሞች በተጨማሪ ለሠራተኞች የሞራል ድጋፍ የሚሰጥ እና የሙያ ዕድገት ዕድሎችን የሚያመቻች መሆን አለበት፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም “ሽልመቱ ይበልጥ ሰርተን የህዝባችንን የመልማት ፍላጎት የምናሳካበት እንጂ የሚያዘናጋን አይደለም” ብለዋል። አያይዘውም እውቅናው በቀጣይ በጀት ዓመት አልቆ በመስራት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ አደራም ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review