ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
ባሳለፍነው ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች ጋር ዓመታዊ የስራ ግምገማ አድርጎ ነበር። በዚህ ወቅት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋን የ2017 ዓ.ም አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት አቅጣጫ አብራርተዋል፡፡ በማብራሪያቸው፣ በበጀት ዓመቱ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ የተገኙ ውጤቶች መኖራቸውን አውስተው፣ ውጤቶቹ ዝም ብሎ የመጡ አለመሆናቸውን፣ ዝርዝር ዕቅድ ተይዞና የጋራ ተደርጎ በብርቱ ጥረት መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በከንቲባዋ ማብራሪያ መሠረት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም መሻሻሎች መጥተዋል፡፡ በተለይ በከንቲባ ፅህፈት ቤት እና በከተማዋ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ በኩል ግልፅ የሆነ እቅድ ተይዞ እስከታች ድረስ ባሉት መዋቅሮች እንዲተገበሩ መደረጉ ለተገኘው ውጤት ተጨማሪ አቅም ነው፡፡
በከተማዋ ምክር ቤት በኩልም በተለይ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ ጥብቅ የሆነ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን የጠቆሙት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ ቋሚ ኮሚቴዎች እያንዳንዱን ከፍለ ከተማ እና ወረዳ ወርደው ከህዝብ ጋር በተጨባጭ እየተገናኙ ክትትል አድርገዋል፡፡ ስራዎችን በመፈተሽ እና በማረጋገጥ ግብረ መልስ በመስጠት ከተማዋን ለተሻለ ውጤት አብቅተዋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ዋና ኦዲተርም ተቋማትን አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ በግልፅ ኦዲት ማድረግ እንዲችል ሁኔታዎች ተመቻችተውለት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የሰው ኃይሉን እንዲያሰፋ፣ ተቋሙ ጥርስ ያለው እንዲሆን ማድረግ፤ የምክር ቤት ፎረም ተቋቁሞ እያንዳንዱ ተቋም በኦዲት የተገኘበትን ውስንነት እንዲያስተካክል፣ ምላሽ መስጠትና ተጠያቂነት ማስፈን እንዲችል ተደርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል ያሉትን የአሰራር ክፍተቶች ክትትል በማድረግ የተሰጡ ግብረ መልሶች መኖራቸውንም ጠቅሰው፣ በፀረ ሙስና ግብረ ኃይልም ሆነ በፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል ክትትል የተደረገባቸው እና የአሰራር ክፍተቶች ተለይተው እንደ ግብዓት ተወስደዋል። የህዝብ መድረክ ተፈጥሮ በየደረጃው ጥቆማዎች መምጣት እንዲችሉ ተደርጓል። በዚህ መልክ የመጡ የህዝብ ጥቆማዎች እንደ ግብዓት ተወስደው ተጠያቂ የሚሆነው እንዲጠየቅ እየተደረገ የሄደበት አግባብ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡
ከሁሉ በላይ የህብረተሰቡን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ዝርዝር እቅዶች በበጀት ዓመቱ በተያዙት ልክ ታቅደው 95 በመቶው ተከናውነዋል ያሉት ከንቲባዋ፣ በተለይ የኑሮ ውድነትና የገበያ መዛባትን ለማስተካከል በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በዚህ በጀት ዓመት የተሰሩ ስራዎች ቀላል አይደሉም ብለዋል።
ነጥቡን ሲያብራሩም፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ህገ ወጥ ንግድን መቆጣጠር፣ የእሁድ ገበያን ማስፋፋት፣ በድጎማ፣ በምገባ መርሃ ግብሮች እና በሌሎች አገልግሎቶችም ችግሩን ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የመንግስት ሰራተኞች ማዕድ በማጋራት፣ በየተቋማቱ ካፍቴሪያዎችን በመክፈት፣ የሸማቾች ሱቆችን በማስፋፋት የወገኖችን ጫና ማቅለል ተችሏል፡፡ በቀጣይ ዓመትም ይህን ማድረግ ዋነኛው ትኩረታችን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በዚህ ዓመት ብቻ በርካታ ሼዶች ተሰርተው ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ የኮሪደር ልማት ብቻ ከ5 ሺህ በላይ ሱቆችን የመስራት ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህም ለከተማዋ ነዋሪዎች ተላልፎ በኑሮ ውድነት ቅነሳው ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን እና ልማት ቢሮ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በእርግጥ መቀናጀት ጀምረዋል ብለውም፣ ይህ ጅምር የበለጠ መጠናከር አለበት የሚለው ነጥብ መያዝ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የአንድ መሶብ ማዕከል ወደ አገልግሎት ሲገባ የቅንጅት ችግር በመሠረታዊነት እንደሚፈታ ጠቁመው፣ ነገር ግን ቅንጅታዊ አሰራሩ በዋናነት ሊረጋገጥ የሚችለው በአመራሩ ቁርጠኝነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የከተማዋ የፕላን እና ልማት ቢሮ፣ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ መሬት ምዝገባ፣ ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ተቀናጅተው ካልሰሩ በስተቀር የከተማዋን መሠረተ ልማት ማረጋገጥ ላይ ክፍተት ይፈጠራል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ሌሎቹ ከቅንጅት ክፍተት አንፃር ውስንነት እንዳለባቸው የተነሱ ተቋማት ሲሆኑ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ረገድ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሁለቱ ተቋማት የመቀናጀት ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ተቋማቱ ኃላፊነታቸውን በቅጡ ለመወጣት ተቀናጅተው እየተናበቡ በጋራ መስራት እንዳለባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
የቆዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች ጉዳይ እንዴት ይታያል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከንቲባዋ ምላሽ ሲሰጡ፣ በመንግስት እና የግል አጋርነት የሚሰሩትን ቤቶች ጨምሮ ቆጣቢዎችን ታሳቢ ያደረገ አካሄድ ተዘርግቷል፡፡ በማህበር ተደራጅተው የወጡ አሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ሊስተናገዱ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተነጋግረናል፡፡ የቤት አቅርቦትን መጨመር አንዱ ትኩረታችን ነው ብለዋል፡፡
የፈረቃ ትምህርት ቤቶች አሁንም በከተማዋ ቢኖሩም በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 150 የትምህርት ፕሮጀክቶችን ገንብተን ወደ አገልግሎት አስገብተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ አሁን የፈረቃ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር ወደ 11 አውርደናል፡፡ እንዲህም ሆኖ የተማሪው ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 100 ሺህ ገደማ ተማሪ ነው የጨመረው፡፡ ሆኖም ግን ትምህርት ቤቶቹ መቀበል ካለባቸው ተማሪ ብዛት በላይ ሳይቀበሉ በእስታንዳርዱ መሠረት ብቻ ይመዝግቡ፡፡

እያንዳንዱን ጉዳይ ስንፈፅም ምን ያህል ከሌብነት በፀዳ ነው? የሚለው ጉዳይ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ምላሽ ማግኘት ያለበት ነጥብ እንደሆነ ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡ “ህዝብን በየስራው ማሳተፍ ለዚህ ይረዳል፤ በተለይ ህዝቡ ዐይንና ጆሮ እንዲሆነን ተቀራርቦ መስራት ይበጃል። የሌብነት ድርጊት ሲፈፀም ያየ ሰው በምን አግባብ መጠቆም አለበት? ይህን በማድረጉ ተጋላጭ እንዳይሆንስ እንዴት ከለላ ይደረግለታል? የሚለውን መለየት ያስፈልጋል”፡፡
የቆዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈታታቸውን ጠቅሰው፣ ዘንድሮም በእቅድ ላይ የተመሰረተ አሰራር መከተል ያስፈልጋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች እየተፈቱ መሄድ አለባቸው፡፡ የተፈቱትም ህዝቡ ጋር ደርሰው እውቅና ማግኘት አለባቸው፡፡
የመሬት ፋይሎች በሚገባ ዲጂታላይዝድ ተደርገዋል፡፡ እንደ ድሮው ፎርጂድ ፋይል አደራጅቶ ማስገባት የሚቻልበት ዕድል ተዘግቷል፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት ነው የሚል ነጥብም አንስተዋል ከንቲባዋ፡፡
“የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ነዋሪዎች ቀን ያወጣ ነው” ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች በንፁህ ቤት እና አካባቢ ውስጥ የመኖር ዕድል አስገኝቷል። ለህፃናት፣ ለወጣቶች፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለጤና ጣቢያዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። መሰረተ ልማት አሟልቷል፤ ንግድን አነቃቅቷል፣ የቱሪዝም መስህብን አስፋፍቷል፤ ሁለተኛው ዙር ብቻውን በመቶ ሺህ የሚቆጠር የስራ ዕድል ፈጥሯል፤ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ ደግሞ ይህ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል፡፡
“ከሰላምና ፀጥታ አንፃር ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል፤ መባላቱ ይብቃ፤ ለልማት መረዳዳት ያስፈልጋል በሚል ጉዳይ ላይ የሁሉም አቋም አንድ መሆን አለበት” ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ “በተለይ በየደረጃው ያለ አመራር በዚህ ረገድ ጠንክሮ መስራት አለበት፡፡ በከተማዋ ከሚታዩ አንዳንድ አዝማሚያዎች አንፃር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፤ ከህዝብ ጋር ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የሀሰት መረጃዎች በተበራከቱበት በዚህ የሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ስራ መጠናከር አለበት፡፡ እያንዳንዱ አመራር ኮሚኒኬተር መሆን ይኖርበታል፤ በሚሰራው ስራ ዙሪያ በቂና አስፈላጊውን መረጃ የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል፡፡ እውነት እንዲሸፋፈን ዕድል መፍጠር የለበትም ሲሉ አክለዋል፡፡
“የቀጣይ በጀት ዓመት ትኩረቶቻችን ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር የሚያስችል በአመለካከት መላቅ፣ ወቅቱን የዋጀ ሀሳብ ማመንጨትና ችግር ፈቺነት ያስፈልጋል፤ አደረጃጀቶችን በስነ ምግባር እና በተግባር ምሳሌ በሚሆን ልክ ማጠናከር፣ አመራርን በማጥራት መገንባት፣ ማብቃት ይገባል” ብለዋል፡፡
የተጀመረውን የተቋማት ግንባታ ማጠናከር ቁልፍ ስራ ነው የሚሆነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ተቋማቱን በአሰራር፣ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ “የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምም ውጤታማ አድርገን የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሶብን ማሳከት ይገባል”፡፡
“350 ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች ቋሚ የስራ ዕድል እንዲያገኙ እንሰራለን። ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ግንባታ በቀጣይም ትኩረት ማግኘት አለበት። ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ የኑሮ ውድነትን ማቃለልም ተተኳሪ ስራ ይሆናል፡፡ የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋት፣ የንግድ ሱቆችን መገንባት፣ ተኪ ምርቶችን አምርቶ መላክ፣ የገቢ አሰባሰብን ከሰው ንክኪ በማውጣት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ፣ የሰው ኃይል ግንባታ፣ የተሰበሰበውን ገቢ በአግባቡ መጠቀም፣ የቱሪዝም ዘርፍ፣ የከተማ ውበት፣ ፅዳት፣ አረንጓዴ ሽፋንና ሰው ተኮር ስራዎች፣ የትምህርትና ጤና ተደራሽነት፣ የጤና ቱሪዝም ወደ ተግባር ይገባል፤ የትራንስፖርት ዘርፉን ማሻሻል፣ በጥቅሉ የሰው ልጆችን ክብር ያስቀደሙ የልማት ስራዎች ውሃ እና ቤትም ይተኮርባቸዋል” ብለዋል፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ