መዲናዋ በብሉምበርግ የከተሞች ውድድር

You are currently viewing መዲናዋ በብሉምበርግ የከተሞች ውድድር

“ሀሳብ ማመንጨት የሚችል የከተማ ስርዓትና አመራር እየተገነባ ስለመሆኑ ምስክር ይሆናል”

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢንጂኒዬር)

ከተሞች ከህዝብ ቁጥር መጨመርና በዚያው ልክ እያደገ ከሚሄድ ፍላጎት ጋር ተያይዞ ውስብስብ ፈተናዎች እያጋጠሟቸው ይገኛል፡፡ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ተደራሽነት፣ ድህነት፣ የአየር ብክለት፣ የወንጀል መስፋፋት እና ሥራ አጥነት ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ለመፍታት እና የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

አዲስ አበባ ከተማም እያጋጠሙ ላሉ ፈተናዎች ምላሽ ለመስጠት፣ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹ የሆነች ከተማ እንድትሆን ለማስቻል መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ ፕሮጀክቶችን በመገንባትና በሌሎችም ዘርፎች ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡

በከተማዋ እየመጡ ያሉ ለውጦችም በነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር ምስጋና እየተቸራቸውና እውቅና እያገኙ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ ብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የተሰኘው ተቋም በሚያዘጋጀው የብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የከንቲባዎች ውድድር (2025 Mayor’s Challenge) አዲስ አበባ ከመጨረሻዎቹ 50 የፍፃሜ ተወዳዳሪዎች መካከል አንዷ ሆናለች። መዲናዋ ይህንን ደረጃ ያገኘችው በዓለም አቀፍ ደረጃ በመርሃ ግብሩ ለመወዳደር ካመለከቱ 630 ከተሞች መካከል ተመርጣ እንደሆነ ተቋሙ በገፀ ድሩ ይፋ አድርጓል፡፡

በብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ አማካኝነት የሚዘጋጀው ይህ ውድድር ከተሞች ለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች የሚወስዱትን ችግር ፈቺ የመፍትሔ እርምጃ፤ በመረጃ ላይ የተመሰረተ እና ሊሰፋ የሚችል መሆኑን መለየት እና መደገፍን ያለመ ነው። የዘንድሮው ውድድርም የከተሞችን ፈርጀ ብዙ ችግሮችን በአዲስ የፈጠራ ሃሳብ በመፍታት ሰው ተኮር የሆነ የከተማ ትራንስፎርሜሽንን ማምጣት መቻል ላይ ያተኮረ ነው። በዚህም አዲስ አበባ ዘመናዊ፣ የተቀናጀ እና በአንድ ማዕከል የተደራጀ የመረጃ ስርዓትን በመጠቀም የነዋሪዎቿን ችግሮች ለመፍታት ባቀረበችው የመወዳደሪያ ዝክረ ሃሳብ ተመርጣለች። የአዲስ አበባ ከተማ የፈጠራ ልዑክ ቡድንም በቦጎታ ኮሎምቢያ እየተካሄደ ባለው የብሉምበርግ የውድድር ሃሳቦች ካምፕ መገኘቱን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢንጂኒዬር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ላለፉት አንድ ዓመት አካባቢ ከ33 ሀገራት የተውጣጡ 630 ከተሞች የተሳተፉበት ውድድር ላይ አዲስ አበባ ያቀረበችው ሀሳብ ገዥ ሆኖ ከ50ዎቹ የመጨረሻ ተወዳዳሪዎች ውስጥ መግባቷ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

በተለይም በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ እውቅና እያገኘች መምጣቷ እንደ ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ከተማዋ ለውጥ እያመጣች መሆኗን፣ የከተሞችን ፈተናዎች ለመፍታት ሀሳብ ማመንጨት የሚችል የከተማ ስርዓትና አመራር እየተገነባ መሆኑን ምስክር ይሆናል ነው ያሉት፡፡

አዲስ አበባ በብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የከንቲባዎች ውድድር ላይ ይዛው የቀረበችው ሀሳብ በተለይ ለህዝብ የሚቀርቡ የመንግስት አገልግሎቶችን እንዴት ማዘመን ይቻላል? የሚለው ላይ እንደሚያተኩር ያነሱት ወንድሙ (ኢንጂኒዬር)፣ ከበርካታ ከተሞች ተወዳድራ ከ50ዎቹ ውስጥ መግባቷም በፕሮጀክት ደረጃ የቀረበውን ሀሳብ ወደላቀና የሚተገበር ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል፡፡  በተቋሙ አማካኝነት ከተሞች ሀሳባቸውን የሚያቀርቡበት የሀሳብ ሜዳ (Idea Camps) የሚዘጋጅ ሲሆን፤ በዚህም በቴክኒክ ባለሙያዎች ሀሳቦችን የመገምገም፣ ድጋፍና ክትትል እንዲያገኙ ለማድረግ ዕድል ይፈጠራል፡፡

እንደ ወንድሙ (ኢንጂኒዬር) ገለፃ፣ አዲስ አበባ በትላልቅ መድረኮች ላይ መሳተፏ ዓለም አቀፋዊ እውቅናን ያስገኝላታል፡፡ በከተማዋም የመንግስት አገልግሎቶችን ፈጠራ በታከለበት መንገድ ለመስጠት እየተደረገ ላለው ጥረት እውቅና የሚሰጥ ነው፡፡ በተለይ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ፣ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ በመረጃ ትስስርና ሌሎች አገልግሎትን ማዘመን ላይ የሚሰሩ ስራዎችን በማጠናከር ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች መፍታት ያስችላል፡፡

በከተማዋ የሚሰሩ ስራዎችና የሚሰጡ ውሳኔዎች መረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑም  በከንቲባ ቢሮ ስር ማዕከላዊ የሆነ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ጥናትና ምርምር ማድረግ፣ ዕቅዶችን ማጥራት የሚያስችል እንደ ቤተ ሙከራ የሚያገለግል “ሲቲ አክሽን ላብ” የተሰኘ ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ እንደሚገኝ ወንድሙ (ኢንጂኒዬር) ገልጸዋል፡፡ ይህ ማዕከልም በርካታ ጥቅሞች እንደሚኖሩት አብራርተዋል፡፡

 በከተማዋ በተለያዩ ጊዜያት ጥናቶች ይደረጋሉ፡፡ እነዚህ ጥናቶችም ወደ ፖሊሲ ተቀይረው እንዲተገበሩ ያስችላል። ጥናትና ምርምር፣ ፖሊሲና ትግበራን በማገናኘት በተለይ ከቤት ልማት፣ ከመሬት አጠቃቀም፣ አካባቢ ጥበቃ፣ መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳል ብለዋል፡፡

“በከተማዋ የሚሰሩ ስራዎች የተቋማትን ቅንጅት የሚጠይቁ ናቸው” ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ ተቋማት በጋራ ተቀናጅተው የሚሰሩ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ ይህ ማዕከልም በተቋማት መካከል የሚኖረውን ቅንጅት፣ ትስስርና ተደራሽነት ለማሻሻል ይጠቅማል፡፡ ቀጣይነት ያለው እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የከተማ ልማት ስራ ለማከናወን ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡

ወንድሙ (ኢንጂኒዬር) እንደገለፁት፤ የከተማዋን ውስብስብ የሆኑ ችግሮች በተበታተነ የአስተዳደር ስርዓትና ደካማ በሆነ የመረጃ መሰረተ ልማት መፍታት አይቻልም፡፡ የተቀናጀ፣ ጥናትና ምርምር፣ ፖሊሲና ትግበራ ማካሄድ የሚቻልበት ማዕከል ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባ የመጨረሻ 50 ከተሞች ውስጥ መግባቷም ይህንን ሀሳብ ማሳደግ የሚቻልበት መነሻ ገንዘብ አግኝታለች ማለት ነው። በውድድሩም ወደ 25 ከተሞች ውስጥ ከገባች ተጨማሪ ገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ታገኛለች፡፡

በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የብሉምበርግ የከንቲባዎች ውድድር ከሁሉም አህጉራት ካሉ ከተሞች ተሳትፎን የሚስብ ትልቅ ዓለም አቀፍ ውድድር ሲሆን፤ በዚህ ዓመትም ከምርጥ 50 ከተሞች መካከል ቶሮንቶ፣ ሴኡል፣ ኬፕ ታውን፣ ሲያትል፣ ሳን ፍራንሲስኮ፣ ቫንኮቨር፣ ቡዳፔስት፣ ማርሴይ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ እና ሌሎችም ከተለያዩ አህጉራት እንደሚገኙበት የብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ መረጃ ያመለክታል።

እነዚህ 50ዎቹ የመጨረሻ የፍፃሜ ተወዳዳሪዎች ዓለም አቀፍ በሆኑ ባለሙያዎች የቴክኒክ ድገፍ እየተደረገላቸው ቆይተው የመወዳደሪያ ሃሳቦቻቸውን ያዳብራሉ። የመወዳደሪያ ሀሳባቸውን በሚተገበር መልኩ ቀርጾ ለማቅረብ እያንዳንዳቸው 50 ተወዳዳሪዎች 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ይሰጣቸዋል፡፡ በመጨረሻም የሚመረጡት 25 ተወዳዳሪዎች ችግር ፈቺ የሆኑ ሃሳቦቻቸውን የሚተገበር አድርጎ ለመቅረፅ የሚያግዝ የአንድ ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እያንዳንዳቸው የሚያገኙ ይሆናል።

ብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ በዓለማችን ባለፀጋ ከሆኑ ቢሊየነሮች አንዱ በሆኑት ማይክል ብሉምበርግ የተቋቋመ በበጎ አድራጊነት የሚሰራ ድርጅት ሲሆን፤ በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ 700 ከተሞች እና 150 ሀገራት በመንቀሳቀስ የሰዎችን ህይወት የሚያሻሽሉ ስራዎችን ይደግፋል፡፡ በዋናነትም በአምስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሀብት በመመደብ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ትምህርት፣ ኪነ-ጥበብ፣ አካባቢ ጥበቃ፣ የመንግስት ኢኖቬሽንና የህዝብ ጤና ይጠቀሳሉ፡፡ በፈረንጆቹ 2014 ብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለከተሞች ድጋፍ አድርጓል፡፡

የብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የከንቲባዎች ውድድር ከተሞች ያሉባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት፣ የነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል አዳዲስ ፈጠራዎችን መተግበር እንዲችሉ የመደገፍ ዓላማ አለው፡፡ ፕሮግራሙ ከተለምዷዊ አሰራር በመውጣት ከተሞች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለመወጣት እና የህዝብ አገልግሎትን ማጠናከር ላይ እንዲሰሩ መሪዎችን ያበረታታል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review