ህብረተሰቡ ለተከላ በነቂስ የሚወጣውን ያህል እንክብካቤው ላይም መበርታት እንደሚገባው ተጠቁሟል
በድህነት ለተሳለቁብን፤ ‘ከዚያ ካላችሁበት አረንቋ አትወጡም፣ የብልጽግናን ሽታ አታዩትም፣ መልማት አይቻላችሁም፣ መሻገር አይሆንላችሁም፣ ለእናንተ የተገባ እና የተፈቀደ አይደለም’ ላሉንሁሉ፤ ሕዝብ ከወሰነ፣ ሀገር ከወሰነ፣ ምን ማድረግ እንደሚቻል፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም፣ አረንጓዴ ዐሻራም ያሳያሉ።” የሚለው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 2016 ዓ.ም ያስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡ ዓባይ “የበይ ተመልካች” ሆነን የቆየንበት ሀብታችን ነው፡፡ እራትና መብራት ይሆነን የነበረው ዓባይ፣ እሱነቱን ብቻም ሳይሆን ለም አፈራችንን ጭምር በመያዝ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ሲሳይ ሆኖ አገልግሏል። ለዘመናት የተሰራው የዲፕሎማሲ ጫና ደግሞ ግራ ቀኝ እንዳናይ፣ የውስጥ መሻታችንን ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዳንቀይር እግር ከወርች አስሮን ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የአሁኑ ትውልድ ሲወስን የማይቻል የሚመስለውን ችሎ አሳይቷል፡፡ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ የግድቡ ግንባታ ላይ ዓሻራውን አሳርፏል፡፡ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ሆነ ተቋማት የእውነታውን ጥግ እና የፍትሐዊነቱን ልክ እንዲረዱ ያለመታከት ሰርቷል፡፡ በመጪው ወርሃ መስከረም 2018 ዓ.ም ፕሮጀክቱ የሚመረቅ መሆኑ ደግሞ የውሳኔውን ፍሬ በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡
አረንጓዴ ዓሻራውም በዚሁ ልክ የሚቃኝ ነው፡፡ መረሃ ግብሩ 2011 ዓ.ም ከመጀመሩ በፊት 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ባለፈው ዓመት በተደረገው ጥናት መሰረት ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ እንዳለ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ለተገኘው ውጤት ምስጢሩ በጋራ መወሰንና መነሳታችን ነው፡፡ በችግኝ ተከላው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እየተሳተፈ ለመሆኑ ደግሞ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ሁነኛ አስረጂ ነው፡፡ ከሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በተዘጋጁት የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በርካታ ችግኞችን በመትከል ዓሻራውን ሲያሳርፍ ቆይቷል። ዘንድሮም ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ቀጠሮ ተይዟል፡፡
እንደ አዲስ አበባ በመርሃ ግብሩ መጀመሪያ ዓመት ማለትም በ2011 ዓ.ም የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሐምሌ 22 የተካሄደ ሲሆን አዲስ አበባ በእለቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ችላለች፡፡ በቀጣዩ ዓመት ሐምሌ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በተከናወነው የአንድ ጀንበር መርሃ ግብር ደግሞ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በ2013 ዓ.ም ምንም እንኳን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ያንዣበበበት ዓመት ቢሆንም በአንድ በኩል የበሽታውን ስርጭት የመግታት በሌላ በኩል አሻራን የማኖር ስራ ለመከወን ርብርብ በመደረጉ ሐምሌ 4 በተካሄደው መርሃ ግብር 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ መትከል የተቻለበት ዓመት ሆኗል፡፡ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት ማለትም በ2014 ዓ.ም 4 ሚሊዮን፣ በ2015 ዓ.ም ከ4.5 ሚልዮን በላይ፣ በ2016 ዓ.ም ከ9 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፡፡
በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የሆልቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር አቶ መክብብ ማሞ ለዝግጅት ክፍላችን የሰጡት አስተያየት ይኼንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ “የአረንጓዴ ዓሻራው ከመጀመሩ በፊት ችግኝ ለህብረተሰቡ እስከ በር ድረስ የማቅረብ ስራዎች ይሰሩ ነበር፡፡ አሁን ላይ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ መጥቷል፡፡ በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ በርካታ ነዋሪ በመሳተፍ፣ መርሃ ግብሩም እንደ ዓመታዊ ፕሮግራም በመያዝ ላይ ይገኛል” የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ የዘንድሮው መትከያ ቀን ተለይቶ ከመገለጹ በፊት “መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ ማህበረሰቡ ይጠይቅ ነበር። ይህ በህብረተሰቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት ከመፍጠር አንጻር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመዲናዋ ዝግጅት እንዴት ያለ ነው?
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ መንግስቱ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፣ “መዲናዋ ለአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል አቅዳለች። ለዚህ ደግሞ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች 271 የመትከያ ቦታዎች ተለይተው ካርታ የማዘጋጀት ስራ (ጂኦ ሪፈረንስ) ተከናውኗል፡፡ ለዘንድሮው የችግኝ ተከላ ካፈላናቸው 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞች በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙትን ባሉን 11 የችግኝ ጣቢያዎች በማስቀመጥ ለተከላው ዝግጁ የማድረግ ስራም ተሰርቷል” ብለዋል፡፡
የመትከያ ቦታዎቹ ተለይተው ካርታ የማዘጋጀት፣ እያንዳንዱ የተከላ ቦታ ላይ ሪፖርት የሚያደርግ አንድ አንድ ባለሙያ የማመቻቸት ስራ መሰራቱ የዘንድሮውን የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ከዚህ በፊት ከነበሩት መሰል መርሃ ግብሮች ለየት እንደሚያደርገውም አክለዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ የዘንድሮው ከዚህ በፊት ከነበሩት በቁጥር ያነሰው ከተማዋ ለአረንጓዴ አሻራ ያዘጋጀችው ካሬ እየተሸፈነ በመምጣቱ ነው።
የችግኝ ተከላ ግብ መትከል ሳይሆን ማጽደቅ እንደሆነ የገለጹት የሆልቲካልቸር ልማት ዳይሬክተሩ አቶ መክብብ፣ “በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የተከላቸው ችግኞች በምን መልኩ እንደተተከሉ መሬት ላይ ወርዶ የማረጋገጥና የማስተካከያ እርምጃ የመውሰድ፣ የችግኝ ፕላስቲኮችን በተገቢው ሁኔታ የማስወገድ እና መሰል ስራዎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ይጠበቃል” ሲሉ ስላስተዋሉት ትዝብት እና መደረግ ስላለበት ተግባር አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
“እንደ ቢሮ ያለው ግምገማ፣ የችግኞችን ላስቲኮች በአግባቡ ቀድዶ በማውጣት መትከል፣ ላስቲኮቹ አካባቢውን እንዳይበክሉ ሰብስቦ ማስወገድ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ያመላክታል” ሲሉ የአቶ መክብብን አስተያየት የሚያጠናክሩት ወይዘሮ ስንታየሁ፣ ዘንድሮ ተከላው ካለቀ በኋላ የእንክብካቤ ማህበራት አሉ፤ እነሱን በማሰማራት የማስተካከያ ስራ ይሰራል። አፈር ያነሰበት ቦታ አፈር የመጨመር፣ ላስቲኮቹን ሰብስቦ ወደ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ የመውሰድ፣ ድጋፍ የሚፈልጉ ችግኞች ካሉ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ የሚያስችል ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላው ህብረተሰቡ ዝናብ፣ ብርድ… ሳይል በነቂስ ወጥቶ በአብሮነትና በጥሩ ስሜት የሚተክለው በመሆኑ በርከት ያሉ ችግኞችን ለመትከል ዕድል ይፈጥራል። ይህን ታሳቢ በማድረግ በዘንድሮው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ አንድ ሰው አምስት ችግኝ ይተክላል በሚል ታሳቢ ተደርጎ በመርሃ ግብሩ ላይ 248 ሺህ 322 ሰዎች እንደሚሳተፉ በዕቅድ መያዙንም ዳይሬክተሯ አክለዋል፡፡
ሁለቱም ዳይሬክተሮች ለጽድቀቱ ውጤታማነት በተከላው ለሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ይስማማሉ፡፡
ዕፅዋት ተመጣጣኝ የአየር ልውውጥ እንዲኖርና የሚያስፈልገንን ኦክስጅን እንድናገኝ የሚያደርጉን፣ ከፋብሪካዎችና ተሽከርካሪዎች የሚወጣውን የካርበን ዳይ ኦክሳይድ ልቀትና ግሪን ሃውስ ጋዞችን ወደ ራሳቸው ወስደው ለእኛ የምንተነፍሰውን ኦክስጅን የሚያመርቱልን ናቸው፡፡ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿም ሆነ ለእንግዶቿ ምቹ በማድረግ ረገድም አይተኬ ሚና አላቸው የሚሉት አቶ መክብብ፣ ከተከላ እስከ ድህረ ተከላ ያለውን ፕሮግራም በጋራ ማሳካት ይቻል ዘንድ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ወይዘሮ ስንታየሁ በበኩላቸው፣ “መትከል ግብ አይደለም፤ መጽደቅም አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የተከልናቸውን ችግኞች የመንከባከብ ኃላፊነት አለብን። ለተከላ በነቂስ የምንወጣውን ያህል እንክብካቤው ላይም መበርታት ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለተከላ በተዘጋጁት ጉድጓዶች ላይ የመትከል ልምድ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ አካፋና ዶማ የምናዘጋጀው ጎድጓዶቹ ከአንድ ወር በፊት ቀድመው የተቆፈሩ በመሆናቸውና ደለል ሊሞላቸው ስለሚችል አፈር ማውጣት እንዲቻል ነው፡፡ ሆኖም ህብረተሰቡ ቀድሞ ወደተዘጋጀው ስፍራ ገብቶ ከመትከል ይልቅ ፊት ለፊቱ ያገኘውን ቦታ በመቆፈር የመትከል ልምድ አለው፤ ይህ መስተካከል አለበት” ብለዋል፡፡ በዕለቱ ማለትም ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ህብረተሰቡ በነቂስ እና በንቃት እንዲሳተፍ አስቀድሞ ባሉት ቀናት የድምፅ ማጉያ በመጠቀም ጭምር ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰራም አክለዋል፡፡
በምህረቱ ፈቃደ