የአረንጓዴ ልማት አርበኛ

You are currently viewing የአረንጓዴ ልማት አርበኛ

“በመኖሪያ ቤቴ ፊት ለፊትና በአካባቢው ያለው ስፍራ በተለይ ለህፃናት ምቹ ያልነበረ፣ ቆሻሻ መጣያ፣ መፀዳጃና ለሌሎችም አላስፈላጊ ተግባራት ይውል ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ህፃናት ለተለያዩ ተላላፊ በሽታ ይጋለጡ ነበር” ይላሉ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በሻሌ ብሎክ 35 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ትክክል ገና፡፡

አቶ ትክክል ይህን ለመኖሪያ የማይመችና ለህፃናት ጤና ጠንቅ የሆነ የአካባቢ ገፅታ ሲመለከቱ እረፍት ከመንሳትም ባለፈ አካባቢውን ፅዱና አረንጓዴ የማድረግ ፍላጎት አደረባቸው። ይህንንም ማድረግ እንደሚፈልጉ ለወረዳው አስተዳደር ሃሳባቸውን አጋሩ። ወረዳውም መልካም ሃሳባቸውን በመቀበል በአካባቢው ለአረንጓዴ ስፍራ የተለየውን 5 ሺህ 728 ካሬ ሜትር ቦታ ጭምር እንዲያለሙት ፈቀደላቸው፡፡ 

አቶ ትክክል ከዚያ በኋላ ያለውን ስራ፣ “የአካባቢው ነዋሪዎች ሃሳቤን ተረድተው አብረውኝ ለማልማት ፈቃደኛ ሆኑ። የልማት ኮሚቴ በማቋቋምም በ2010 ዓ.ም ወደ አረንጓዴ ልማቱ ስራ ገባሁ” ሲሉ ነበር ያጫወቱን፡፡ 

የግቢ ማሳመሪያ (የተለያዩ የአበባ ዝርያዎች)፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ቃሪያና ሌሎች ተክሎችን በመኖሪያ ግቢያቸው  በመትከል አረንጓዴ ስፍራ ያደረጉት አቶ ትክክል፣ ይህን ልምድ በመጠቀምና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ቆሻሻ መጣያና መፀዳጃ የነበረውን አካባቢ ወደ አረንጓዴነት መቀየር የሚያስችል ስራ ሰርተዋል፡፡ ጥድና ሌሎች ተክሎች እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ዘይቱና ተክለዋል፡፡ የህፃናትና የአዋቂዎች መዝናኛ ስፍራም ተሰርቷል፡፡ የመኖሪያ መንደሩን ከነዋሪው ጋር በመሆን አረንጓዴና ውብ ከማድረግ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሀገር በከተማ ግብርና ዘርፍ ላይ እንዲሰራ ያስቀመጡትን አቅጣጫ በመከተል ካሮት፣ የሀበሻ ጎመን፣ ቃሪያ፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ስኳር ድንች፣ ቀይ ስር… በማልማት ለአካባቢው ነዋሪ የእለት ፍጆታው ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በስፍራው በመገኘት የልማት ስራውን በመመረቅ እውቅና እንደሰጡ እና በአረንጓዴ ልማት ስራውም አድናቆታቸውን እንደገለፁ አቶ ትክክል ይናገራሉ፡፡ በ2017 ዓ.ም ደግሞ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ “የውበትና አረንጓዴ ልማት አምባሳደር” በሚል እውቅና ማግኘታቸውን ገልፀውልናል፡፡ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ትክክል በእንዲህ አይነቱ ስራ ላይ የባለቤታቸው ድጋፍ እንዳልተለያቸውም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

የውበትና አረንጓዴ ልማት አምባሳደሩ አቶ ትክክል፤ የሰፈሩ ገፅታ ከቆሻሻነት ወደ ፅዱነት  እንዲቀየር፣ በአረንጓዴ ተክሎች ተውቦ እንዲታይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከጅማሬው እስከ አሁን ድረስ በየዓመቱ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ በዘንድሮው መርሃ ግብርም 100 ችግኝ ለመትከል በዝግጅት ላይ መሆናቸውንና የአረንጓዴ ልማት ስራውን ከነዋሪው ጋር በመተባበር የበለጠ የማስፋት ርዕይ እንዳላቸውም ነግረውናል፡፡

አቶ ሮቤል ክብረት የአካባቢው ነዋሪ ሲሆኑ ስለ አቶ ትክክል ያላቸውን አስተያየት እንዲህ ይገልፃሉ፡፡ “አቶ ትክክል ቀድሞ ቆሻሻ መጣያ፣ መፀዳጃ እንዲሁም የሌቦች መሸሸጊያ የነበረን ስፍራ በግል ተነሳሽነት የአካባቢውን ነዋሪ በማስተባበር፣ ኮሚቴ በማዋቀር  እንዲፀዳ፣ እንዲለማና አረንጓዴ እንዲሆን ያስቻሉ ግለሰብ ናቸው፡፡ እኔም ባለኝ አቅም ለአረንጓዴ ልማቱ የበኩሌን ተሳትፎ እያደረግሁ እገኛለሁ፡፡

አካባቢው የቀድሞ ገፅታው ተቀይሮ ለህፃናትና ለአዋቂዎች የመዝናኛ ስፍራ እንዲሆን  እንዲሁም ለማህበራዊ አገልግሎት እንዲውል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በተጓዳኝም ነዋሪውንና የተዋቀረውን ኮሚቴ በማስተባበር በከተማ ግብርና የጓሮ አትክልቶች ለአብነት ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ቃሪያ በማልማት ተጠቃሚ እንድንሆን ያደረጉ፤ መልካም የልማት ስራ የሚሰሩና ለሌሎች ግለሰቦች ዓርአያ የሚሆኑ ናቸው” ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡

በክፍለ ከተማው የውበትና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት የከተሞች አረንጓዴነት ልማትና ውበት ቡድን መሪ አቶ የሸዋልዑል ማንደፍሮ እንደገለፁት፤ በክፍለ ከተማው በህብረተሰብ ተሳትፎ ጭምር የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በመሆኑም 1 ሺ 400 የማህበረሰብ ክፍሎች 72 ሄክታር የሚሆን አካባቢ በአረንጓዴ ልማት እንዲሸፈን አድርገዋል፡፡ 120 ማህበራትን በማሳተፍ ደግሞ 65 ሄክታር አረንጓዴ ስፍራዎች፣ አደባባይና የመንገድ አካፋዮች እንዲሁ አረንጓዴ በማድረግ እንክብካቤ እየተደረገ ይገኛል፡፡

አካባቢያቸውን አረንጓዴ ለሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚሰራ ነው ቡድን መሪው የጠቆሙት፡፡ በክፍለ ከተማው በአስር ወረዳዎች በሚገኙ ባለሙያዎች ተክሎች መቼ መከርከም እና ውሃ መጠጣት እንዳለበት እንዲሁም ኮምፖስት በምን መልኩ እንደሚደረግ ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ቦታው አረንጓዴነቱን ይዞ እንዲቀጥልም ክትትል ይደረጋል፡፡ በክፍለ ከተማው እንደ አቶ ትክክል ዓይነት በአረንጓዴ ልማት ስራው አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም እውቅና እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር እንዳሻው ከተማ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ፤ ቢሮው የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን ተከትሎ ለአረንጓዴ ስፍራ የተለዩ ቦታዎችን አረንጓዴ በማድረግ ለዜጎች ምቹ፣ በአረንጓዴ ልማቷ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነች ከተማን መፍጠር ላይ ዓላማ ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባን አረንጓዴ የማድረግ ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ በስፋት በመስራታቸው ከ2010 ዓ.ም በፊት ከነበረው 2 ነጥብ 8 በመቶ የአረንጓዴ ሽፋን በ2017 በጀት ዓመት ከ22 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡

ኢንጂነር እንዳሻው እንዳስረዱት፤ ከተማዋን አረንጓዴ የማድረግ ስራ ሲጀመር ህብረተሰቡ፣ ግለሰቦች፣ የመንግስትና የግል ተቋማት፣ የግል ባለሃብቶች በአረንጓዴ ልማት ስራው እንዲሳተፉ የማንቃት፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች በሰፊው ተሰርተዋል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስራው ሲከናወን በዋናነት ማህበረሰቡን ባለቤት በማድረግና በማሳተፍ ነው። ህብረተሰቡም አካባቢውን አረንጓዴ እንዲያደርግ፣ እንዲንከባከብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል፡፡ ህብረተሰቡ የአረንጓዴ ልማት ስራውን በየአካባቢው ሲሰራ በምን አይነት ዲዛይን ቢሰራ የተሻለ ይሆናል የሚለውን በማዘጋጀት የመስጠትና የመደገፍ ስራ ሲሰራም ቆይቷል፡፡

በአረንጓዴ ልማት ስራው ሞዴል የሆኑ ግለሰቦችንም የማበረታታት፣ እውቅና የመስጠት እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት አምባሳደር በማድረግ እየተሰራ ነው። በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ 36 ሺህ 761 የማህበረሰብ ክፍሎች በአረንጓዴ ልማት ስራቸው እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን ከ450 ሄክታር በላይ በማህበረሰቡ መልማታቸውን ኢንጂነር እንዳሻው ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ አሁን በኮሪደርና በአረንጓዴ ልማቱ ስራ ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ እየሆነች ትገኛለች፡፡ በዚህ ተግባር ላይ መንግስት ከሚያከናውነው ባለፈ የተቋማት፤ የሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፎ የተገለጠበት ነው፡፡ አቶ ትክክል ገናም ነዋሪውን በማስተባበር የመኖሪያ አካባቢያቸውን አረንጓዴና ማራኪ እንዲሁም ለኑሮ ምቹ ያደረጉ ባለውለታ በመሆናቸው ሌሎች ግለሰቦች ልምዳቸውን በመውሰድ ፅዱና አረንጓዴ አካባቢን መፍጠር ይገባቸዋል መልእክታችን ነው፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review