በአማራ ክልል የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰላምን በዘላቂነት ማስከበር የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ የክልሉ ምክር ቤት አፈ -ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው መክፈቻ ላይ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ እንደተናገሩት፣ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
የፍትህና የዳኝነት ስርዓቱን ማሻሻል የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው፣ ከ10 በላይ አዋጆች ፀድቀው በስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉንም አውስተዋል።
በአስፈፃሚው አካል ላይ የተጠናከረ ክትትል በማድረግ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም እየተሻሻለ ከመምጣቱም ባሻገር፣ ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቁ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በክልሉ የሰፈነውን ሰላም በማፅናት የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስፈፃሚው አካል በጠንካራ ቅንጅት መስራት እንደሚገባው ጠቁመው፣ ምክር ቤቱም የቅርብ ክትትል በማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።
ጉባዔው ከሐምሌ 19 እስከ 23 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።