በክልሉ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥና ልማትን የማፋጠን ስራዎች በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም ርእሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት የ11 ወራት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ ቀርቧል።
ርእሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው፤ በክልሉ የጽንፈኛ ቡድኖች የጥፋት እንቅስቃሴ ለዜጎች ማህበራዊ እንቅስቃሴ ፈተና ሆኖ እንደነበር አስታውሰዋል።
በመሆኑም በመንግስት በተወሰደ የተጠናከረ የህግ ማስከበር እርምጃ እና የሰላም ጥሪ ጭምር አሁን ላይ በብዙ አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀስ በነበረው ጽንፈኛ ቡድን ላይ በተወሰደው እርምጃ የጥፋት አጀንዳው ከሽፎ የሎጀስቲክስና የሰው ሃይሉ ተዳክሞ እየተበታተነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በየቀኑ እየገቡ መሆኑን አንስተዋል።

አሁንም ቢሆን የሰላምን አማራጭ ለሚቀበሉት እድሉ ያለ መሆኑን ተናግረው ለጥፋት በሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የክልሉን ሰላምን ከማፅናት በተጓዳኝ በቂ ግብዓትና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ፣ የዜጎችን የስራ ዕጥነት ችግር የመፍታትና የፕሮጀክቶችን የስራ አፈፃፀም ማፋጠንም ትኩረት ይደረግበታል ብለዋል።
የገበያ ማረጋጋት፣ የገቢ አቅምን ማሳደግ፣ የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት፣ የማዕድን ሃብቱን አልምቶ መጠቀምና ሌሎችም የልማት ስራዎች ይጠናከራሉ ሲሉ ማስረዳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የትምህርትን ጥራትና ተደራሽነት በማረጋገጥ እንዲሁም የጤናውን ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን በቀጣይ በትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት እንደሆኑም አንስተዋል።
ምክር ቤቱም በርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው ሪፖርት ላይ በጥልቀት በመወያየት በቀጣይት በሌሎች አጀንዳዎችም ላይ የሚመክር ይሆናል።