በሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ላይ ለመሣተፍ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና እንግዶች አዲስ አበባ በመግባት ላይ ያገኛሉ።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጀሲካ አሉፖ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቷ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስትባበሪያ ማዕከል ሀላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ከሐምል 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያም ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶችን እየተቀበለች ይገኛል።
ይህን ዓለም አቀፍ ሁነት ኢትዮጵያ እና ጣልያን በጋራ የሚያዘጋጁ ሲሆን የስርዓተ ምግብ ሽግግር እና ትራንስፎርሜሽን ጉባኤው የሚያጠነጥንበት አበይት አጀንዳ ነው።
የምግብ ስርዓት ጉባኤው በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም በጣልያን ሮም የተካሄደው የመጀመሪያ የተመድ የምግብ ስርዓት ላይ የተገቡ ቃሎች ትግበራ ሂደትን መነሻ በማድረግ የሚካሄድ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ቀዳሚ ትኩረቱ ከመጀመሪያው ጉባኤው በኋላ የምግብ ስርዓትን አስመልክቶ ያሉ ለውጦችን የሚዳስስ ሲሆን በጉባኤው ላይ ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን አስመልክቶ ያገኟቸውን ስኬቶች እና ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ሪፖርት እንደሚያቀርቡም ይጠበቃል።