በመዲናዋ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ በመገባቱ በምርት አቅርቦት፣ ህጋዊ ንግድ ስርዓትና ግብይት በማስፈን እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገልጸዋል።
በከተማዋ አቅርቦትን በማሻሻል እና ህገ-ወጥ ንግድን በመከላከል ገበያን ለማረጋጋት እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በየደረጃው የ9ዐ ቀናት እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን፣ ከማዕከል እስከ ወረዳ ግብረ-ሃይል እና ቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
የገበያ ማረጋጋት፣ ህግ ማስከበር እና ኢትዮጵያ-አዲስ አበባ ታምርት በሚል የተቋቋመው ግብረ ሀይል ከሰኔ እስከ ሐምሌ 15 ያለውን የስራ እንቅስቃሴ ገምግሟል።
ግብረሀይሉ ባደረገው እንቅስቃሴ በወር ከ15 ቀን በምርት አቅርቦት፣ ህጋዊ ንግድ ስርዓትና ግብይት በማስፈን፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል መቻሉን ነው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ የገለጹት።
በተለይ ህብረት ስራ ማህበራት በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ መደረጉ እና በንግድ ስራዎች ድርጅትና በሌሎች የሚቀርቡ ምርቶች ነዋሪዎች ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል።
በከተማዋ በተገነቡና ወደ ስራ በገቡ ገበያ ማዕከላት ምርቶች እንዲቀርቡ በመደረጉ የዋጋ መሻሻል መታየቱንም አንስተዋል።
ግብረሀይሉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ያሉት አቶ ጃንጥራር፣ ለአብነትም የእንቁላል ዋጋ ከ20 ብር በላይ የነበረው አሁን ከ14 እስከ 16 ብር እንዲሸጥ መደረጉን አንስተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ፣ የሰብል ምርት አቅርቦት በሸማች ህብረት ስራ ማህበርና በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ በስፋት እንዲቀርቡ ተደርጓል ብለዋል።
በተለይም ማህበራት ያላቸውን ቦታዎች ከኪራይ እንዲያስለቅቁና እሴት ጨምረው ራሳቸው ዳቦ እና እንጀራ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ መደረጉን አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ያለንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የነበሩ ነጋዴዎች እና ያልታደሰ ንግድ ፈቃድ ይዘው የሚሰሩትን ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲገቡ ተደርጓ ብለዋል፡፡
የምሽት የንግድ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን አንስተው፣ የነዳጅ ግብይት ላይ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመሆን በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ በከተማዋ ህጋዊ የንግድ ስርዓት እና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
በሳምንት ሁለት ጊዜ የመጋዘንና የነዳጅ ማደያ ፍተሻ እንደሚደረግ የገለፁት ወ/ሮ ሊዲያ፣ ያለ አግባብ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም ድንገተኛ ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
ግብረ-ሀይሉ በቀጣይም የምርት አቅርቦት እጥረት፣ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር እና ህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል።
በሄለን ጀምበሬ