በመዲናዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት በስራቸው ላይ የነበረውን ጫና እንደቀነሰላቸው የመንገድ ጽዳት ባለሙያዎች ተናገሩ

You are currently viewing በመዲናዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት በስራቸው ላይ የነበረውን ጫና እንደቀነሰላቸው የመንገድ ጽዳት ባለሙያዎች ተናገሩ

AMN- ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመለወጥ እና ከማስዋብ ባሻገር፣ ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ምቹ የስራ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል፡፡

በተለይም የከተማዋን ውበትና ንጽህና ለመጠበቅ በመንገድ ጽዳት ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ሚናው የላቀ ነው፡፡

በመዲናዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የነበረባቸውን የስራ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰላቸው የመንገድ ጽዳት ባለሙያዎች ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ከመብራት ሀይል- የረር ድልድይ ድረስ በመንገድ ጽዳት ባለሙያነትና በአስተባባሪነት እየሰሩ የሚገኙት አቶ ዘላለም መብራቱ፣ የኮሪደር ልማቱ ለመንገድ ጥርጊያ ሰራተኞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በምንሰራበት መስመር ላይ ከተለያዩ የንግድ ተቋማት፣ ከመኖሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች የተለያዩ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ወደ መስመር ይጣሉ ነበር የሚሉት አቶ ዘላላም፣ አሁን የኮሪደር ልማቱ ከተሰራ በኋላ እነዚህ ነገሮች በእጅጉ ቀንሰዋል ብለዋል፡፡

አቶ ዘላለም አክለውም፣ የኮሪደር ልማቱ ከመሰራቱ በፊት በህገ ወጥ ነጋዴዎች አማካኝነት በመንገድ ላይ የሚጣሉ የአትክልት እና ሌሎች ተረፈ ምርቶች በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድሩ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 7 መብራት ሀይል- የረር መስመር የጽዳት ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ገነት ጥላዬ፣ ከዚህ በፊት በምንሰራበት መንገድ ላይ የነበረው አቧራ፣ ጭቃ እና ጥሩ ያልሆነ የመንገድ ላይ ሽታ አሁን ላይ ታሪክ ሆኗል፤ በዚህም የሰራተኛው የስራ ተነሳሽነት ጨምሯል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመንገድ ላይ ይቆሙ የነበሩ ከትንንሽ እስከ ትላልቅ መኪኖች ለጥርጊያ ስራው እንቅፋት እንደነበሩ የሚገልጹት ወይዘሮ ገነት፣ ኮሪደር ከለማ በኋላ ያለ ስራ መስመር ላይ የሚቆም መኪና ባለመኖሩ ስራችንን በነፃነት ለመስራት አስችሎናል ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ጎሮ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የኮሪደር ልማት የመንገድ ጽዳት ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ሀብታም ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ ከዚህ በፊት ሰርተን ስንመለስ የተሰራ አይመስልም ነበር፣ አሁን ግን የሚያስመሰግን ሥራ እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ በቀሪ መንገዶችም ቢስፋፋ ከተማዋ ውብና ንጽህናዋ የተጠበቀ ትሆናለች ሲሉም ሰራተኞቹ ገልጸዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review