በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ዛሬ ይጀመራል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዛሬውን የጉባኤ መክፈቻ ቀን የተግባር ቀን ሲል ሰይሞታል።
የዛሬው የጉባኤው ውሎ ነገ እና ከነገ በስቲያ ለሚደረጉ ዋነኛ የጉባኤው ውይይቶች እንደ መክፈቻ እና መግቢያ የሚቆጠር ነው።
የጉባኤው ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በምግብ ትራንስፎርሜሽን እያከናወነቻቸው የሚገኙ ስራዎችን በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ስፍራዎች ይጎበኛሉ።
የጉብኝቱ ዓላማ የኢትዮጵያን የስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ተሞክሮ ለተቀረው ዓለም ማካፈል እንደሆነ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል።
ከመስክ ምልከታዎቹ በተጨማሪ በርካታ የጎንዮሽ ሁነቶች ይካሄዳሉ።
ከሁነቶቹ መካከል ኢትዮጵያ እና ጣልያን በጋራ በመሆን በሳይንስ ሙዚየም የአፍሪካን የቡና ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ማሻሻል ላይ ያዘጋጁት ከፍተኛ የምክክር መድረክ አንዱ መሆኑን ኢኒስቲትዩቱ ገልጿል።
በውይይቱ ላይ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ)፣ የዓለም አቀፉ የቡና ድርጅት(ICO)፣ የአፍሪካ የቡና ድርጅት(IACO) እና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ይሳተፋሉ።
ውይይቱ በአፍሪካ የቡና ስርዓት የእሴት ሰንሰለቶችን ለማጠናከር በተወሰዱ እርምጃዎች የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ትኩረት ያደርጋል።
ለቡና ምርት፣ ማቀነባበር እና ንግድ የሚያስፈልግ ዘላቂ የፋይናንስ አማራጮችን መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል።
መንግስታት፣ የቡና አምራቾች፣ የልማት ኤጀንሲዎች፣ የኢንዱስትሪ ተቋማትና ሌሎች ተዋንያንያን በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እና ፍትሃዊነትን ማዕከል ያደረገ የቡና ስርዓት መፍጠር ላይ ያላቸውን የጋራ ቅንጅት ማጠናከር ላይ ይመክራሉ።
በሁነቱ ላይ የኢትዮጵያ የቡና አፈላል ስነ ስርዓት ለተሳታፊዎቹ ይቀርባል።
ኪነ ጥበብ እና የወጣቶች የመፍጠር አቅም ዘላቂ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ከመፍጠር አንጻር ያላቸውን ሚና አስመልክቶ የተዘጋጀ ውይይት ይደረጋል።
ወጣቶች የለውጥ ወኪል በመሆን በስርዓተ ምግብ ያላቸውን ሚና ማሳደግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል።
ወጣቶች ስርዓተ ምግብን ለመቀየር ያላቸውን ህልም እና መሻት በስዕላዊ መግለጫ ያቀርባሉ።
ባህል በስርዓተ ምግብ ውስጥ ያለው ድርሻም ውይይት የሚካሄድበት አጀንዳ ነው።
በተጨማሪም የጉባኤው ተሳታፊዎች ስርዓተ ምግብ፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ ሀገር በቀል የስርዓተ ምግብ መፍትሄዎችና የፋይናንስ ሞዴሎች የእውቀት እና የልምምድ ልውውጥ ያደርጋሉ።
ለስርዓተ ምግብ የተቀረጹ ሀገር በቀል አማራጮችን ከዘላቂ ልማት ግቦችና ከአየር ንብረት ለውጥ ግቦች ጋር ማስተሳሰርን የተመለከቱ ሀሳቦችም ይቀርባሉ።
የተግባር ቀን ከሀልዮታዊ እሳቤዎችና ከቃል ንግግሮች ባለፈ በስርዓተ ምግብ ላይ የተግባር እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባ ጠንካራ ማሳሰቢያዎች እንደሚተላለፉ ከኢዜአ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።