በሁለቱ ሀገራት መካከል በድንበር አካባቢ በተከሰተው ግጭት ፤ የካምቦዲያ እና የታይላንድ መሪዎችን ማነጋገራቸውን እና ሁለቱም ሀገራት አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚፈልጉ ፕሬዚዳንት ትራምፕ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ኘሬዝዳንቱ ስኮትላንድን በጎበኙበት ወቅት ነበር በማህበራዊ ድረ-ገፃቸው ላይ ጦርነቱ እንዲቆም እንደሚፈልጉ የገለፁት ፤ ይህ ካልሆነ ከሁለቱም የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ጋር የንግድ ስምምነቶችን እንደማይፈፅሙ አስጠንቅቀዋል።
በታይላንድ እና ካምቦዲያ ድንበር ላይ ያለው ግጭት ከተጀመረ ሶስተኛ ቀኑ መሆኑ ታውቋል።
በደቡብ ምስራቅ እስያ ጎረቤቶች መካከል በተደረገው ግጭት ፤ ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ130,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገልጿል ።
በአሜሪካ ዋሽንግተን የሚገኙት የታይላንድ እና የካምቦዲያ ኤምባሲዎች ፤ ግጭቱን የተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አለመስጠታቸው ተዘግቧል ።
በግጭቱ አሁን ላይ አንድ የታይላንድ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ፤ ወደ ጊዜያዊ መጠለያነት የተቀየረ መሆኑን አንድ በጎ ፈቃደኛ ተናግሯል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የታይላንድ አምባሳደር ትናንት በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት ፤ ከሀምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በታይላንድ ግዛት ውስጥ ወታደሮች በተቀበሩ ፈንጂዎች መቁሰላቸውን አሳውቋል ። ነገር ግን ካምቦዲያ ይህን ጉዳይ ማስተባበሏ ተገልጿል ።
በብርሃኑ ወርቅነህ