2ኛው የተባበሩት መንግሥታት ሥርዓተ-ምግብ ጉባኤ ተሳታፊዎች በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሥር የሚገኘውን የጥራት መንደር በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ጎብኚዎችን አቀባበቀል በማድረግ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ የምርቶችንና የአግልግሎት ጥራት ማረጋገጥ የሚያስችል አስተማማኝ ብቃት ያላቸውን ተመጋጋቢ የጥራት መሰረተ-ልማቶችን ያቀፈ ግዙፍ የጥራት መንደር ገንብታ ወደ ሥራ ማስገባቷን ገልጸውላቸዋል፡፡
በጥራት መንደሩ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ፣ ወደ ውጭ ሀገራት የሚላኩ እና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን የጥራት ደረጃ የመፈተሽና ተስማሚነት የማረጋገጥ ተግባራት እንዲደሚከናወኑም ለእንዶቹ አብራርተውላቸዋል፡፡
አቶ አንዳለው ኢትዮጵያ የሥርዓተ-ምግብ ሽግግር ከማረጋገጥ በተጓዳኝ የምግብ ጥራትና ደህንነት የማረጋገጥ ሥራዎችን በጥራት ማረጋገጫ መሰረተ-ልማትና በዘመናዊ የላብራቶሪ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የስርዓተ-ምግብ ጉባኤ ተሳታፊዎቹ በጥራት መንደር ከሚገኙ የጥራት ማረጋገጫ መሠረተ-ልማት ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅትን፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩትን እና የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩትን ከጎበኙ በኋላ ባዩት ነገር መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗንም ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡