ሁለተኛው የተመድ የምግብ ስርዓት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወኗን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በእጅጉ በማሳደግና የሌማት ትሩፋትን በመሳሰሉ በርካታ የልማት መርሃ ግብር በመላ ሀገሪቱ ሁሉንም ባቀናጀ መልኩ ባከናወነቻቸው ተግባራት አመርቂ ዉጤት ማስመዝገቧን አስገንዝበዋል።
ጉባኤው በ2ኛ ቀን ውሎው በዓለም የምግብ ሥርዓት ላይ በተገኙ ለውጦች፤ እንዲሁም ዘርፉን እየፈተኑ በሚገኙ ተግዳሮቶች ላይ በስፋት ምክክር ይደረጋል።
ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት በምግብ ስርዓት ዘርፍ ያላቸውን ልምድ፣ መምጣት ያለባቸውን ለውጦች እና እየታዩ የሚገኙ ለውጦችን ለማስቀጠል የሚረዱ እርምጃዎችን የያዙ ቁልፍ መልዕክቶችን በጉባኤው እያቀረቡ ነው።
በኢትዮጵያ እና ጣልያን አዘጋጅነት በተሰናዳው በዚሁ ጉባኤ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተጨማሪ የሌሎች ሀገራት መሪዎችም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የጣሊያን ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ፣ የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሃመድ፣ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ፣ የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ፕሬዝዳንት አልቫሮ ላሪዮ፣ የተባበሩት መንግሥታት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የዩኤንዲፒ የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ መሃሙድ፣ የኬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶን ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮች እና ሌሎችም ባልድርሻ አካላት ንግግር አድርገዋል፡፡
በጉባኤው ያልተገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቪድዮ ለጉባኤው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመጀመሪያው የምግብ ስርዓት ጉባኤ በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም በጣልያን ሮም መካሄዱ ይታወሳል። በወቅቱ ቃል የተገቡ ዝርዝር ጉዳዮች በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛው ጉባኤ ላይ የአፈፃፀም ሂደቱ ይገመግማል።
በጉባኤው ላይ ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንን አስመልክቶ ያገኟቸውን ስኬቶችና ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች በተመለከተ ሪፖርት ያቀርባሉ።
ይህ የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ዋናው ግቡ የምግብ ሥርአቶች ለውጥን በማረጋገጥ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት በመሆኑ፤ ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት እና ትብብርን በሁሉም ዘርፎች ለማጎልበት ያግዛል ተብሎም ግምት ተሰጥቶታል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች፣ የሁለትዮሽ ውይይቶች እና ጉብኝቶች ይደረጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
በይታያል አጥናፉ