(ክፍል አንድ)
በምሽት የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የወጣው ደንብ ቁጥር 185/2017 በያዝነው ዓመት ከወጡ በርካታ ደንቦች መሀከል አንዱ ሲሆን በአራት ክፍሎች እና በአስራ አራት አንቀጾች ተዋቅሮ በአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ፀድቆ ከመጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ደንብ በርካታ ዓላማዎችን አንግቦ የተቋቋመ ደንብ ሲሆን እነዚህንም አላማዎች በደንቡ የመግቢያ ክፍል ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ ጽሑፍም የመጀመሪያ ክፍል ላይ የምንዳስሳቸዉ ይሆናል፡፡
ይህ ደንብ በርካታ ዓላማዎችን አንግቦ የተቋቋመ ደንብ ሲሆን እነዚህንም አላማዎች በደንቡ የመግቢያ ክፍል ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ ጽሑፍም የመጀመሪያ ክፍል ላይ የምንዳስሳቸዉ ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አሁን ከደረሰችበት ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ለውጥ አንፃር የአብዛኛው ማህበረሰብ የሥራ ባህል እና ፍላጎት በመለወጥ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የንግድ ሥራዎችንና አገልግሎቶችን በምሽት መከወን እየተለመደ የመጣ ተግባር ሆኗል፡፡ እንደሚታወቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበረሰቡ በምሽት የመንቀሳቀስ እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም በምሽት ጭምር አገልግሎቶችን የመስጠት ዝንባሌዎች እየተስተዋለ መጥቷል። ይህም የሚያሳየው የማህበረሰቡን የለውጥ ሂደት እንዲሁም የኢኮኖሚውን መነቃቃት ሲሆን የስራ ባህልንም ከማዳበር አንፃር የራሱን የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማችን አዲስ አበባ በርካታ ፕሮጀክቶች ተነድፈው በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ፕሮጀክቶች በባህሪያቸው ቀን እና ሌሊት የሚከናወኑ ሲሆን ፍጻሜያቸውም ውጤታማ ነው፡፡ ከነዚህ ፕሮጀክቶች ባህሪም እንደምንረዳው የስራ ባህላችንን ቀይረን ቀንም ማታም ከሰራን ሀገራችን ወደምትገባበት ከፍታ እንደምንወስዳት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ያደጉት ሀገራት አሁን ያሉበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ ያላቸው ጠንካራ የስራ ባህል የራሱ የሆነ ሚና ይጫወታል፡፡
ሀገራችን አሁን ካለችበት የድህነት አረንቋ ለማውጣት አሁን ላይ እየተነቃቃ እና እየዳበረ ያለውን የስራ ባህል ቀጣይነት እና ወጥነት ያለው እንዲሆን እና አዲስ አበባ መዲናችንም የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የዲፕሎማቲክ መቀመጫ እንደመሆኗ ከሌሎች መሰል ከተማዎች ጋር ተወዳዳሪ እና የሚገባትን የእድገት ደረጃ እንዲሁም ስታንዳርድ ለማላበስ አሁን ላይ ያለው ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ቀጣይነት እውን ለማድረግ እንዲሁም ወጥነት እንዲኖረው ቀን ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በምሽት የንግድ እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም እንዲሁ በምሽት ተግባራቸውን ማከናወን የሚችሉበትን የአሰራር ሥርዓት በህግ መደንገግ በማስፈለጉ ደንብ ቁጥር 185/2017 ተቋቁሞ በስራ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ደንብ ክፍል አንድ ትርጓሜ የሚያስፈልጋቸውን በደንቡ ውስጥ የተካተቱ ቃላቶች ትርጉም የተሰጠባቸው ሲሆን፤ በዚህ መሰረት “የንግድ ተቋም” ማለት ንግድ ሥራ ፈቃድ በማውጣት በከተማው መንገድ ዳር የንግድ ሥራ የሚሰሩ የንግድ መደብሮች እንደሆኑ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም “የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋም” ማለት በከተማዋ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ለመስጠት በቢሮው የተመዘገበና የኦፕሬተርነት ፈቃድ የተሰጣቸው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደሆኑ ደንቡ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ደንብ መሰረትም “አገልግሎት ሰጪ ተቋማት” ማለት በከተማው አስተዳደር ውስጥ በመንገድ ዳር ያሉ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን እንደሚያካትት ደንቡ በግልጽ ይደነግጋል፡፡ እነዚህን እና መሰል አሻሚ ቃላት የደንቡ የትርጓሜ ክፍል ላይ ትርጓሜ ሰጥቶባቸው ይገኛል፡፡
በደንብ ቁጥር 185/2017 መሰረት የንግድ እና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግዴታ ምንድን ነው?
በደንብ ቁጥር 185/2017 ክፍል ሁለት የንግድ እና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግዴታ በዝርዝር የተቀመጠ ሲሆን፤ እነዚህንም ግዴታዎች ከአንቀጽ 4 እስከ አንቀጽ 7 ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ መሰረት በደንቡ አንቀጽ 4 ላይ የምናገኘው ግዴታ የንግድ ተቋማት የሥራ ጊዜን የሚመለከት ግዴታ ነው፡፡
በደንብ ቁጥር 185 አንቀጽ 4(1) መሰረት ማንኛውም የንግድ ተቋም በቀኑ ክፍለ ጊዜ ሲካሄድ የነበረው የንግድ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ዘወትር ማታ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3፡30 ድረስ የንግድ ተቋሙን ለተገልጋይ ክፍት በማድረግ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንዳለበት አንቀጹ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሰረትም ማንኛውም የንግድ ተቋም በምሽት ክፍለ ጊዜ አገልግሎቱን በሚሰጥበት ወቅት ከምሽቱ 3፡30 በፊት የንግድ ተቋሙን መዝጋት እንደማይቻል በግልጽ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የንግድ ተቋማት በምሽት ክፍለ ጊዜ ንግድ ተቋሙን ክፍት ሲያደርግ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ሲቀርብ የነበረውን አገልግሎት ወይም ምርት በተሟላ ሁኔታ በምሽት ክፍለ ጊዜም ለተገልጋይ ማቅረብ እንዳለባቸው ደንቡ ያዝዛል፡፡
አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው የንግድ ተቋማት የአገልግሎት ጊዜያቸውን እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ብሎም እስከ እኩለ ሌሊት ጭምር አገልግሎቶችን የመስጠት ሁኔታ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ እየዳበረ የመጣው የስራ ባህልም ወጥነት ኖሮት በህግም የተደገፈ ለማድረግ የንግድ ተቋማት የሥራ ጊዜ በዚህ ደንብ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ የንግድ ተቋም በምሽት ክፍለ ጊዜ የመግቢያ በሩን ዝግ በማድረግ አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ የንግድ ተቋሙ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን የሚያሳይ በመብራት የሚሰራ ምልክት በግልጽ በሚታይ ቦታ ላይ ማስቀመጥ እደሚኖርበት ደንቡ ያስገድዳል፡፡
ምህረት ወ/ማርያም (ዐቃቤ ህግ)
አንባቢዎቻችን ክፍል ሁለትን በቀጣይ ሳምንት ይዘን እንቀርባለን።