የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር በመቀሌ ውይይት እያደረጉ ነዉ

You are currently viewing የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር በመቀሌ ውይይት እያደረጉ ነዉ

AMN ሀምሌ 21/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማጠናከርና ሰላምን ለማጽናት ችግሮችን በንግግር መፍታትና ዘላቂ መፍትሄ መሻት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ተናገሩ።

ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ መስተዳድር የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች መቀሌ ከተማ ተገኝተዋል።

የመገኘታቸው ዓላማም በሰላም ግንባታ ዙሪያ በትግራይ ክልል ከጊዜያዊ አስተዳደሩና ሌሎች የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ለመምከር መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ፤ በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማጠናከርና ሰላምን ለማጽናት ችግሮችን በንግግር መፍታትና ዘላቂ መፍትሄ መሻት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ የግጭትና አለመግባባት ምክንያቶችን በንግግርና መግባባት እልባት ማበጀት ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።

ለሁሉም የምትመችና የበለጸገች ሀገር መገንባት የሚቻለው ሰላምን በማጽናት፣ ልማትን በማጠናከር መሆኑን ተናግረው ለዚህ ሁሉም የየድርሻውን ሃላፊነት መወጣት አለበት ብለዋል።

የሰላም መሰረቱ የሚጸናው ለሰላምና ልማት መስራት ሲቻል መሆኑን ያነሱት ፓስተር ዳንኤል፤ የግጭትና ጦርነት ምእራፎች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው በንግግር ችግሮችን የመፍታት ባህል መለመድ አለበት ብለዋል።

ከሁሉም ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ተሰባስበን መቀሌ የተገኘነው ይህንኑ ዓላማ ሰንቀን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ልኡካኑ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የምግብ ቁሳቁስና የገንዘብ ጭምር በድምሩ የ43 ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን አሁን ላይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት እያደረጉ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review