ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ

AMN- ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከቤተሰብ ጀምሮ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደች መሆኑን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

የአየር ንብረት ለውጥና የተለያዩ ግጭቶች የዓለም የምግብ አቅርቦትና ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተጠቁሟል።

በፈረንጆቹ 2025 የዓለም የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ሁኔታ ሪፖርት ይፋ ተደርጓል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ የጎንዮሽ ኹነቶች እየተከናወኑ ናቸው።

ከኹነቶቹ መካከል በፈረንጆቹ 2025 የዓለም የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ይፋ ማድረጊያ አንዱ ነው።

በሪፖርቱ ይፋ ማድረጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሪፖርቱ ይፋ ማድረጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣውን የምግብ ዋጋ መናር የጋራ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብለዋል።

የምግብ ዋጋ መናር በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የበለጠ የሚጎዳ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታት ሀገራት የጋራ ትብብርና መፍትሔ ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለይም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋት መርሐ- ግብር ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በሴፍትኔት መርሐ-ግብርም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

በዓለም ላይ አስተማማኝ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ሰላምን ለማፅናት ሀገራት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድ በበኩላቸው፣ በምግብ ዋጋ እየጨመረ መምጣት በርካታ የዓለም ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው እንዳይረጋገጥ ማድረጉን ነው ያነሱት።

የአየር ንብረት ለውጥና የተለያዩ ግጭቶች የዓለም የምግብ አቅርቦትና ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውንም አንስተዋል።

በዓለም በርካታ ህፃናት በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውንም ነው የገለጹት።

በዓለም ላይ ግጭትን ማስቀረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ የጋራ ትብብርና ተግባራዊ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ግጭት ለጤና አስፈላጊ ምግቦች አቅርቦት ላይ እጥረት ፈጥሯል።

ይህ የምግብ ሥርዓት መዛባት በርካታ ዜጎችን ለጤና እክል ተጋላጭ ማድረጉንም አንስተዋል።

የዓለም መንግስታት የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በምግብ ሥርዓት ላይ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል የበለጠ ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ማመላከታቸውንም ተዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review