ዶናልድ ትራምፕ፤ ሩሲያ ከሰኞ ጀምሮ በአስር ወይም አስራ ሁለት ቀናት ውስጥ ከዩክሬን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንድታደርግ ቀነ-ገደብ ወስነዋል ።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ፤ የትራምኘን ጣልቃ ገብነት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው ብለውታል።
ትራምኘ ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሬዝዳንት ፑቲንን ፤ በሀምሳ ቀናት ወስጥ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸውና፤ ይህ ካልሆነ ሩሲያ ከባድ ታሪፍ እንደሚጠብቃት ማሳሰባቸው ይታወሳል።
አሁንም በቀነገደቡ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ፤ በሞስኮ ላይ ማዕቀብ እና ሁለተኛ ደረጃ ታሪፎችን ለመጣል ፍላጎት እንዳለው ትራምኘ ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል ።
ትራምኘ በስኮትላንድ ከእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ፤ በውይይቱ የፑቲንን ድርጊት እንደማይቀበሉት መግለፃቸው ታውቋል።
ኘሬዝዳንት ፑቲን በጊዜ ቀነ ገደቡ ዙሪያ ምንም አይነት አስተያየት ያልሰጡ ሲሆን ፤ የመጀመርያው የሀምሳ ቀናት ቀነ-ገደብ ይፋ ሲደረግ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በጣም ከባድ እና ሞስኮ ይህንን ቀነ-ገደብ ለመተንተን ጊዜ ያስፈልጋታል ሲሉ መናገራቸው ይታወቅ ነበር።
በቱርክ አደራዳሪነት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተካሄደው ሶስተኛው ዙር የተኩስ አቁም ውይይት ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር እስረኞችን ለመለዋወጥ ያስቻለ ሲሆን ፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ግን ምንም አይነት የጎላ ለውጥ አለማምጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
በሩሲያ እና በዪክሬን መካከል ከተደረገው ከሶስት አመት ተኩል አውዳሚ ጦርነት በኋላ ፤ ሁለቱ ወገኖች በአስራ ሁለት ቀናት ውስጥ ጦርነቱን ለማስቆም እንዴት ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ግልፅ አለመሆኑ ታውቋል።
በብርሃኑ ወርቅነህ