የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፣ ከአልጀዚራ እንግሊዘኛው ጋር በነበራቸው ቆይታ አባይ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ሊተዳደር አይችልም ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ከአልጀዚራ እንግሊዘኛው ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አባይ የጋራ የተፈጥሮ ሃብት መሆኑን ገልፀው፣ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት የሚጠቅም የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ መሆን አለበት ሲሉ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ አንድ መቶ ሰላሳ ሚሊዮን ህዝቦቿን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ አባይን እንደ ትልቅ መሳሪያ ተጠቅማ እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያስገድዳታል ሲሉ በአፅንኦት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ 86 በመቶ የሚሆነውን ውሀ ለአባይ ወንዝ አበርክቶ እንዳላት የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አባይ አጠቃላይ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እና ልማትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ያለው የኢትዮጵያ ትልቁ ወንዝ ነው ብለዋል።
የታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ከህዳሴው ግድብ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኙም አብራርተዋል።
ይህም በአባይ ወንዝ የሚከሰተውን ጎርፍ፣ ደለል እና ዉሀው በትነት መልክ እንዳይባክንም ከፍተኛ አስተዋጽኦ መኖሩን በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እየሰራችው ያለው ግድብ ወንዙ ወደ ታችኛዎቹ የተፋሰሱ አገራት እንዳይፈስ አይከለክልም ብለዋል።
ግብፅ የቀደመ የቅኝ ግዛት ስምምነቷን መናፈቋን አቁማ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በፍትሀዊነት እና በዘለቄታዊነት ላይ በተመሠረተ መንገድ ወንዙን መጠቀም አለባት ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአባይን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የኢትዮጵያውያን የረጅም ጊዜ ምኞት እንደነበርም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ግድቡ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የተገነባ ሲሆን፣ ምንም አይነት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ያልተደረገለት መሆኑንም አሳውቀዋል።
በአፍሪካ አህጉር ትልቁ የሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታው ከአስር አመታት በላይ የፈጀ ሲሆን፣ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ፈሰስ ተደርጎበት በመስከረም ወር ላይ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በብርሃኑ ወርቅነህ