ከ58 ሺ በላይ ዛፎች እንዲተከሉ ምክንያት የሆነው የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች

You are currently viewing ከ58 ሺ በላይ ዛፎች እንዲተከሉ ምክንያት የሆነው የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች

AMN – ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም

የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች ሄክቶር ቤልሪን የአየር ንብረት ለውጥ በእጅጉ ከሚያሳስባቸው ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ስፔናዊው የቀኝ መስመር ተከላካይ ያለውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ተጠቅሞ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጠር ይተጋል፡፡

ጉዳዮ አስጨንቋቸው ከሚሰሩ መንግስታዊም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር አብሮ የመስራትም ልምድ አዳብሯል፡፡ በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን በደቆሰበት እ.ኤ.አ 2020 ያካሄደው ዘመቻ ስሙ ከፍ ባሎ እንዲነሳ አድርጎታል ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መቆጣጠር ሲቻል በእንግሊዝ እግርኳስ ያለ ተመልካች እንዲከናወን ፍቃድ ያገኛል፡፡ ቤለሪንም በሰኔ 2020 ’’ ከዋን ትሪ ፕላንትድ ’’ ጋር ዘመቻ ይጀምራል፡፡ አርሰናል አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ 3ሺ ዛፎችን አበረክታለሁ ይላል፡፡ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ አርሰናል ሰባት ጨዋታዎችን አሸነፈ፡፡

በባርሰሎና ያደገው ቤለሪንም በቃሉ መሰረት ሰባቱን ድሎች አንድ አቻን ጨምሮ ስምንት በማድረግ 24 ሺ ዛፎችን አበረከተ፡፡ የተጫዋቹ ተነሳሽነት ያስደሰታቸው የአርሰናል እንዲሁም የሌሎች ክለብ ደጋፊዎችም ተሳተፉ፡፡ በአጠቃላይ 58 ሺ 617 ዛፎች እንዲተከሉ ምክንያት ሆኑ፡፡

ቤሌሪን ከዘመቻው በኋላ ’’ሁሌም የተሻለ ሕይወት መኖር የሚያስችለኝ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያለሁበትን ሞያ ተጠቅሜም ሌሎች ሰዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ እጥራለሁ’’ ሲል ተናግሯል ፡፡

አሁን በሪያል ቤቲስ የሚገኘው ሄክቶር ቤለሪን ጥረት የተሰባሰቡት ዛፎች በማዕከላዊ ብራዚል የተራቆተውን አራጉኢ የብዛ ሕይወት ኮሪደር መልሶ ለም ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ አካል ሆኗል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review