ኢትዮጵያ በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአረንጓዴ ሽፋኗን ያሳደጉ የተፈጥሮ ሚዛንን ያስጠበቁ ውጤቶች እየተዘመገቡ ነው፡፡
የዘንድሮውን ሳይጨምር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በተከለችው ኢትዮጵያ የህብረተሰቡም ተሳትፎ ላቅ ያለ ነበር፡፡
በተለይም 2 ጊዜ ባካሄደችው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከጠዋት እስከ ማታ ሁሉም ኢትዮጵያዊን በማሳተፍ አሻራውን አኑረዋል፡፡
ዘንድሮም 700 ሚሊየን ለመትከል ኢትዮጵያውያን ሀምሌ 24ን በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡

ለዘንድሮው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ አዲስ አበባ ከተማ ያደረገችውን ዝግጅት አስመልክቶ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በከተማዋ ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ 2 መቶ 71 ቦታዎች ተለይተው መዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ ግርማ ሰይፉ የጉድጓድ ቁፋሮ ስራው መጠናቀቁንም አብራርተዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ከ6 መቶ ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሳተፉ የገለጹት ሀላፊው የከተማዋ ነዋሪዎች ለተከላ በተዘጋጁ ቦታዎች አሻራቸውን እንዲኣኖሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በከተማዋ በአንድ ጀምበር ችግኝ ለመትከል የተለያዩ ቦታዎች በቴክኖሎጂ የተደገፉ እና ቆጠራዉም ወደ አንድ ቋት በዚሁ ቴክኖሎጂ ሪፖርት እንደሚደረግ ነው ሃላፊው የተናሩት፡፡
4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኖችን ለመትከል አቅዳ እየሰራች የምትገኘው አዲስ አበባ እስካሁንም የእቅዱ 75 ከመቶ ማሳካቷን አንስተዋል፡፡
በቴዎድሮስ ይሳ