AMN – ሐምሌ 23/2017 ዓ .ም
በክረምት የበጎ ፍቃደኞች ቤታቸው የታደሰላቸው እናቶች ከነበሩበት አስከፊ ሁኔታ መላቀቃቸውን ገልፀዋል።
ቤታቸው ፈራርሶ ጣራያው ዝናብ የሚያስገባ ከመሆኑ ባሻገር፤ በበራቸው ስር ጎርፍ ያስገባ እንደነበር የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ዘይነብ ካሊፋ ያስረዳሉ።
ወ/ሮ ዘይነብ በእንባ በተሞላ ድምፃቸው ስለነበሩበት ሁኔታ ሲያስረዱ፤ ለዓመታት ከአንድ ልጃቸው ጋር የኖሩት ህይወት አስከፊ መሆኑን ይገልፃሉ።

በክፍለ ከተማው የክረምት በጎፍቃደኛ ወጣቶች፣ ባለሀብቶች እና ተቋማትን በማስተባበር እንደ ወ/ሮ ዘይነብ ላሉ እናቶች ቤታቸውን የማደስ ስራ መጀመሩ ተገልጿል።
በበጎ ፍቃደኞች ቤታቸው የታደሰላቸው ወ/ሮ ዘይነብ ፣ይህንን በጎ ተግባር የፈፀሙ አካላትን አመስግነዋል።
ሌላኛዋ ልዩ እንክብካቤ የሚፈልጉትን ባለቤታቸውን ይዘው ለ50 ዓመታት በደሳሳ ቀበሌ ቤት አስከፊ ህይወትን ሲገፉ እንደቆዩ የተናገሩት ወ/ሮ ፅግነሽ ፀጋሁን፣ ይህ ታሪካቸው በክረምት በጎ ፍቃደኞች ቤት እድሳት በነበር ሊተካ ከጫፍ ደርሷል ይላሉ።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ታረቀኝ ኤርሚሾ፣ በክፍለ ከተማው የሚገኙ የቀበሌ ቤቶች ለኑሮ ምቹ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

ሃላፊው ባለፉት አመታት በሰው ተኮር ልማት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ ገልፀው፣ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ የ245 አቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስ እየሰሩ መሆኑን አሳውቀዋል።
ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት በግንባታ ሂደት ላይ ሲሆኑ በተቀሩት ደግሞ ነዋሪዎቹ መግባታቸውን ለማውቅ ተችሏል።
በሔለን ተስፋዬ