የአጼ ፋሲል ቤተመንግሥት እድሳትና ጥገና መንግስት ለባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና ልማት የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing የአጼ ፋሲል ቤተመንግሥት እድሳትና ጥገና መንግስት ለባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና ልማት የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑ ተገለጸ

AMN – ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም

የአጼ ፋሲል ቤተመንግሥት እድሳትና ጥገና ስራ መንግስት ለባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና ልማት የሰጠውን ልዩ ትኩረት እንደሚያሳይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የባህልና ስፖርት ቢሮ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የጎንደር ከተማን የኮሪደር ልማት እና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የቅርስ ጥገና ስራው የሀገርን ሃብት ጠብቆ የማቆየትና ለትውልድ የማስተላለፍ ስራ ነው።

ጎንደር የጥበበኞች የታዋቂ ከያንያንና አርቲስቶች መፍለቂያ ናት ያሉት ሚኒስትሯ የቅርስ እድሳት ስራው ቅርስን ከጥበብ ጋር ያገናኘ ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ አሻራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ትርክት የሚገነባው በጥበብ በመሆኑ መንግስት ለባህል ልማት ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በጥበቡ ዘርፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አንስተዋል።

የኮሪደር ልማት ስራውም የጎንደርን ታሪካዊነት ከጽዳት ከምቾትና ከውበት ጋር ያጣመረ ድንቅ ስራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ሃላፊ ሰይፉ አለሙ፤ በጉብኝታችን ጎንደር በሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን ተመልክተናል ሲሉ ተናግረዋል።

የቅርስ ጥገናና እድሳት ስራውም የህዝቦችን የጋራ ታሪክና ጥበብ ጠብቆ በማቆየት ለታሪክና ለትውልድ የሚያሻግር አኩሪ ተግባር ነው ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፤ በፌደራልና በክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ዘላቂ ሠላምን በማረጋገጥ ለከተማው እድገት መፋጠን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ከፍተኛ አመራሮች የከተማውን የልማት እንቅስቃሴ መጎብኘታቸው የልምድ ልውውጥ ለማካሄድና ተሞክሮን ለማካፈል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review