ኢትዮጵያ ከአምስት አመት በኋላ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እየሰራች እንደምትገኝ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በትምህርት ቤት ምገባ ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንትን አስመልክቶ በተካሄደ ውይይት የኢትዮጵያን ተሞክሮ አቅርበዋል።
በትምህርት ቤት ምገባ አማካኝነት የተመጣጠነ ምግብ ለህጻናት ማቅረብ በተባበሩት መንግስታት በ2030 ዘላቂ የልማት ግቦች ከተቀመጡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል።
ከምግብ ሥርዓት ጋር በተገናኘ አገራት በትምህርት ቤት ምገባ እያከናወኑ ያለው ተግባር ላይ ኢትዮጵያ ያሳየቻቸውን ለውጦችና ሂደቶችም አብራርተዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከውይይቱ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በትምህርት ቤት ምገባ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ካደረጉ ሀገራት አንዷ እንደሆነች ገልጸዋል።
መንግስት ከለውጡ ወዲህ ለትምህርት ጥራት፣ ለልጆች ጤና፣ ለተመጣጠነ ምግብና እኩልነት የተማሪዎች ምገባን እንደ ዋና አጀንዳ በማድረግ ከ2030 አጀንዳ ጋር በማጣጠም እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በእቅዱ መሰረት እ.አ.አ በ2030 ሁሉንም የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በመመገብ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው ብለዋል።
መንግስት እቅዱን ለማሳካት የትምህርት ቤት ምገባን በበጀቱ ውስጥ በማካተት እየሰራ ሲሆን ክልሎችም አላማውን በመረዳት ትኩረት እንደሰጡት ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት እቅዱን ለማሳካት አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩንም ሚኒስትሩ ጨምረዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ ኢትዮጵያን ለማሳደግ ከተያዘው አላማ ጋር በቀጥታ የተገናኘ፣ የሚቀጥለው ትውልድ የሚቀረጽበትና ከድህነት መውጣት የሚቻልበት መርሃ ግብር እንደሆነም ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ አክለውም ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት የተሻለ የሚኖር፣ በአለም ላይ ያሉ ችግሮችን መቋቋም የሚችልና በእውቀት የበለጸገ ትውልድ ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሃመድ በበኩላቸው የትምህርት ቤት ምገባ በዘላቂ የልማት ግቦች ትኩረት ከሰጣቸው ነጥቦች መካካል እንደሆነ አንስተዋል።
ምገባው በቂ ምግብ ከማቅረብ በላይ አካታችና ዘላቂ የምግብ ሥርዓትን በመፍጠር ጤነኛና የተመጣጣነ ምግብ ተደራሽ የሆነ ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት እንዲያገኝ ተደርጓል ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመሆኑም ሀገራት የጀመሯቸውን ተስፋ ሰጪ ስራዎች በማጠናከር በ2030 እቅዱን ለማሳካት በትብብር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።