ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ ዕፅዋትን የመትከል ስራ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተመላከተ

You are currently viewing ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ ዕፅዋትን የመትከል ስራ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተመላከተ

AMN- ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለጥላ እና ለምግብነት የሚውሉ ዛፎች በተሰጣቸው ትኩረት ልክ፣ ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ ዕፅዋትን የመትከል ስራ በትኩረት ቢሰራበት መልካም ነው ሲሉ በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የዕፅዋት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርሃኑ በላይ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ለምግብነት የሚውሉ ዛፎችም መድሃኒትነት እንዳላቸው ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ በአብዛኛው ለመድሃኒትነት ብቻ የሚውሉ ዕፅዋትንም የመትከል ሥራ ትኩረት ቢሰጠው መልካም እንደሚሆን ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ገልጸዋል።

በተለይ በተለየ ሁኔታ ለመድሃኒትነት የሚውሉ ዕፅዋት የመመናመን እና የመጥፋት እድል ያላቸው በመሆኑ፣ እነዚህን የመጠበቅ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በርካታ ሀገር በቀል ዕፅዋትን ጠብቆ የማቆየት ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ ከእነዚህም መካከል ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ ዕፅዋት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

አባቶቻችን ኢትዮጵያን ከስነ ምህዳር አንፃር በረሃ፣ ቆላ፣ ወይናደጋ፣ ደጋ እና ውርጭ በሚል በአምስት እንደሚከፍሏት ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ልክ እንደ ሰው ሁሉ፣ ዕፅዋቱም የሚስማማቸው ስነ ምህዳር መኖሩን አመላክተዋል።

ለመድሃኒትነት የሚውሉትን ዕፅዋት አፈር እና እርጥበትን ጨምሮ የሚስማማቸው የአየር ፀባይ ባለበት ሥፍራ በመትከል ለጤና ከሚሰጡት በረከት ከመቋደስ ባለፈ ዝርያዎቹን ጠብቆ የማቆየት ሥራ መስራት ቢቻል የተሻለ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በሀገራችን ለባህል መድሃኒት እና ለባህል መድሃኒት አዋቂዎች የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ ነው ያሉት ዶክተር ብርሃኑ፣ በሌሎች የዓለም ሀገራት እንደሚደረገው ሁሉ ዘመናዊ እና ባህላዊ መድሃኒቶች ጎን ለጎን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በሚሆኑበት አግባብ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review