በግንባታ ሂደት የሚከሰቱ የሞትና አካል ጉዳት አደጋዎችን ለመቀነስ ለህንጻ ግንባታ ደህነት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመላከተ

You are currently viewing በግንባታ ሂደት የሚከሰቱ የሞትና አካል ጉዳት አደጋዎችን ለመቀነስ ለህንጻ ግንባታ ደህነት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመላከተ

AMN- ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም

የአፍሪካ መዲና በሆነችዉ አዲስ አበባ ግዙፍና ዘመናዊ ህንጻዎች በብዛት እየተገነቡ ነዉ፡፡

በተለይ የኮሪደር ልማቱ ከፈጠረዉ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢ በመነሳት በርካታ ባለሃብቶች፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋመት ለተለያዩ አገልግሎት የሚዉሉ ህንጻዎችን በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

የግንባታው ዘርፍ ለሃገር ከሚያበረክተዉ ኢኮሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር በርካታ ዜጎች በዚሁ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

አቶ ሳህል አወል በአዲስ አበባ ከተማ የአያት አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ላለፉት ስድስት አመታት በግንባታ ስራ ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆን ከቻሉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አቶ ሳህል አወል ከግንባታዉ ዘርፍ ተጠቃሚ ቢሆኑም በአንድ አጋጣሚ በቅርብ በሚያቁት የቀን ሰራተኛ ላይ የደረሰዉን አደጋ ግን መቼም ቢሆን አይረሱትም፡፡

ሰራተኛው እንደወትሮዉ በስራ ላይ እያለ ከሚሰራበት ህንጻ ላይ ወድቆ ሕይወቱ ማለፉን አስታውሰዋል፡፡

ይህ ሰራተኛ ብቻ ሳይሆን በርካቶች በህንጻ ግንባታ ስራ ላይ እያሉ ለሞት፤ ለአካል ጉዳትና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች መዳረጋቸዉን ነዉ አቶ ሳህል አወል ለኤ ኤም ኤን የተናገሩት፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ሀላፊ ኢንጅነር ሰለሞን ተክሌ የሚያረጋግጡትም በጉልበት ስራ የሚተዳደሩ ዜጎች በግንባታ ሂደት ላይ ስለሚደርሰዉ አደጋ በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው የህይወትና የአካል ጉዳት የሚያጋጥማቸዉ መሆኑን ነዉ፡፡

የአዲስ አበባ ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አበበ እሸቱ በበኩላቸዉ፣ የግንባታ ቁሳቁስ አያያዝና አወጋገድ፤ የደህንነት ልብሶችና የኤሌክትሪክ ንክኪ እንዲሁም ጥራቱን ያልጠበቀ የግንባታ መሰረት ለአደጋው መንስኤ መሆኑ በጥናት ተደርሶበታል ይላሉ፡፡

የግንባታ አልሚዎች፣ ኮንትራክተሮችና አማካሪ ድርጅቶች በግንባታ ሂደት ስለደሚደርሰዉ አደጋ ለሰራተኞቻቸዉ በቂ ግንዛቤ አለመስጠታቸዉ ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ የሚደርሰዉ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንዲሄድ ትልቅ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከጥንቃቄ ጉድለትና ከመሰል ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ለሚደርሰዉ ጉዳት ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህግ ድንጋጌ መኖሩን እና ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ ከ24 ሺህ በላይ ህንጻዎች እየተገነቡ መሆናቸውን ያነሱት የአዲስ አበባ ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አበበ እሸቱ፣ ከእነዚህ መካከል የህንጻ ደህንነት መስፈርቱንና ህጉን አክብረዉ የሚሰሩት ከ1ሺህ 688 እንደማይበልጡ ነዉ የተናገሩት፡፡

2ሺህ 920 ህንጻዎች ደግሞ ጉድለት እንዳለባቸው በክትትል ተለይቷል ብለዋል፡፡

በቸልተኝነትና በጥንቃቄ ጉድለት በዜጎች ላይ የሚደርሰዉን ሞትና የአካል ጉዳት ለመቀነስ የግንባታ አልሚዎች፣ ኮንትራክተሮችና አማካሪ ድርጅቶች ለህንጻ ግንባታ ደህንነት ትኩረት ሰጥተዉ ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በአለኸኝ አዘነ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review