በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኞችን ለመተከል በተያዘው መርሐ-ግብር ላይ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ህርያቆስ፣ እጽዋትንና አዝርዕትን በመጠበቅ ልምላሜን ማስቀጠል ከአባቶች የተወረሰ ትውፊት መሆኑን አመላክተዋል።
ብርቅዬ ዕፅዋት በቤተክርስቲያኒቱ አድባራትና ገዳማት እንደሚገኙ ጠቁመው፣ ይህም ቤተክርስቲያኗ ለተፈጥሮ ያላትን በጎ ምልከታ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ፣ ምድር ውብ ሆና ከተፈጠረች በኋላ ጥፋት እንዳትፈጽሙ ይሁን ብሎ አላህ ያስጠነቅቃል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሀዋሪያዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አባ ጴጥሮስ በርጋ በበኩላቸው፣ ከፈጣሪ የተቀበልነው አደራ እጽዋትንና እንስሳትን በመንከባከብ የጋራ ቤታችንን ምድርን እንጠብቅ ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ካውንስል ጠቅላይ ፀሓፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ፣ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በኤደን ገነት ያስቀመጠው እንዲያበጅ እንዲጠብቅ በመሆኑ ተፈጥሮን መንከባከብ እንደሚገባ ገልፀው፣ የወንጌል አማኞች ከ100 ዓመት በላይ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል ሲሉ አክለዋል።
በመካከለኛ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሰበካ መሪ ፓስተር ተሰማ ደሳለኝ፣ አካባቢያችንን መቀየር፣ ማሳመር እና አረንጓዴ ማድረግ ከፈጣሪ የተሰጠን ፀጋ ነው ሲሉ አክለዋል።
ሁሉም የሃይማኖት አባቶች በነገው ዕለት በሚከናወነው የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ህብረተሰቡ በትኩረት እንዲሳተፉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአለኸኝ አዘነ