በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለከመላከል፣ የምግብ ዋስትናንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ- ግብር በ2011 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል፡፡
አዲስ አበባም፣ በ2011 ዓ.ም እንደ ሀገር የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መረሐ-ግብር ስትራቴጅ በመከተል እና የላቀ ትኩረት በመስጠት ላለፉት 6 ተከታታይ ዓመታት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል ችላለች፡፡
አዲስ አበባ ከተማን አረንጓዴ የበለፀገች፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ውብ፣ ከአፍሪካ እህት ከተሞች መካከል ቀዳሚና ተመራጭ ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት እንዲቻል፣ በ2011 ዓ.ም በመዲናዋ 6 ሚሊየን 84 ሺህ 372 ችግኞችን መትከል የተቻለ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም 8 ሚሊየን 513 ሺህ 531 ችግኞች ተተክለዋል፡፡
በ2013 ዓ.ም በመዲናዋ 11 ሚሊየን 441 ሺህ 961 ችግኞች፣ በ2014 ዓ.ም 14 ሚሊዮን 795 ሺህ 595 ችግኞች እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ደግሞ 17 ሚሊየን 445 ሺህ 385 ችግኞች፣ በ2016 ዓ.ም ደግሞ ከ27.7 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል እንደተቻለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በእነዚህ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሚባል ደረጃ የተሳተፉ ሲሆን፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎችም በጋራ ስለ መዲናዋ ገጽታ ግንባታ እና ለጋራ ጥቅም በጋራ መቆምን ለዓለም ያሳዩበት አኩሪ ተግባር ሆኗል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አዲስ አበባ ከተማ ለጀመረችው የዘመናዊ ከተማ ግንባታ ሂደት አንዱ ገጽታ ሆኖ እየተተገበረም ይገኛል፡፡
ይህ ተግባር ከተማዋን አረንጓዴ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን እየተሰራ ከሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በየኮሪደሩ በተዘጋጁ የአረንጓዴ እና የመዝናኛ ስፍራዎች ላይ ለመዲናዋ ውበት እና ድምቀት የሚሰጡ የተለያዩ የእዕዋት አይነቶች በመተከል ላይ ናቸው፡፡
በመርሐ-ግብሩ በመዲናዋ የሚገኙ በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎችን ማልማት የተቻለ ሲሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ በስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተሰፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኘተውበታል፡፡
በተለይ በመዲናዋ እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት እየተተከሉ የሚገኙ ችግኞች የመዲናዋን ውበትና ገጽታ ከማላበስ ባለፈ ጤናማ፣ በአካል የዳበረ እና በመንፈስ የተረጋጋ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የላቀ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመዲናዋን የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሮች አማካኝነት የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከ2.8 በመቶው ወደ 22 በመቶው ማደግ እንደቻለ እና የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት መጠንም ከ85 በመቶው በላይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በአስማረ መኮንን