AMN – ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም
የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ጋር የተሳሰረ መስተጋብር አላቸው። በዘመናት የህይወት ዑደት ውስጥ ተፈጥሮ ለሰው ልጆች መራራም ጣፋጭም ፍሬ እየሰጠች ቀጥላላች።
ከተፈጥሮ የተስማማ እንዲሁም ለተፈጥሮ ዋጋ የሚሰጥ ትስስር ጣፋጭ ፍሬዋን ሲያገኝ፤ ከተፈጥሮ የተቃረነ ጉዞ ደግሞ አስከፊ ዋጋ እያስከፈለ ቀጥሏል።
በየጊዜው የሚዛባ አየር ንብረት፣ የውሃ አካላት መቀነስና ንጥፈት፣ እንዲሁም የዋልታዎች በረዶ መቅለጥ የሰው ልጅን ስልጣኔ እየተገዳደሩት ይገኛሉ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገና የሰው ልጆችን ከተፈጥሮ ጋር የሚያስተሳስር ታላቅ የልማት ስራ ነው።
አረንጓዴ አሻራ ከሁሉም የስራ መስኮች ጋር የተሳሳረ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ሲሆን፤ ነገ ሀገርን ለሚረከቡ ወጣቶች ደግሞ ልዩ ትርጉም ያለው ስራ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ከተፈጥሮ ጋር የታረቀች ሀገር ነገዋ ብሩህ ነውና!
ታዳሽ ኃይልን ዋነኛ የኢነርጂ ምንጯ ለማድርግ ቆርጣ እየሰራች ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶችና የኪነጥበብ ባለሞያዎች፤ አረንጓዴ አሻራ የነገ ህልማቸው ሞተር ከመሆኑም በላይ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ያረጋገጠች ሀገርን እንዲረከቡ መሰረት የሚያስቀምጥ የሀገር ውጥን ነው።
ተፈጥሮ ላይ መስራት በአንድም በሌላም መንገድ ኪነ-ጥበብን መስራት እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ የቲያትር ቤቶች አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ዘገየ ያስረዳሉ።
ለሰባተኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የአንድ ጀንበር አረንጎዴ አሻራ መርሃ ግብር የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ችግኝ ለመትከል ከመዘጋጀት በተጨማሪ ህብረተሰቡን በማነሳሳት ላይ እየሰሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
በሙዚቃ፣ በግጥም፣ በመነባነብና በሌሎች የኪነ-ጥበብ መስተጋብሮች ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ችግኝ እንዲተክል ከማድረግ ባሻገር ከተፈጥሮ ጋር ቁርኝነት እንዲኖረው ያግዛል ብለዋል።
ከተፈጥሮ ኪነ-ጥበብ እንደሚፈልቅ፣ ተፈጥሮንም ለመስራት ለማረም የሰው ልጆችን ግንዛቤን ለማሳደግ ሁለቱም ተመጋጋቢ እንደሆኑ ያስረዳሉ።
ኪነጥበብ መዳረሻው ማህበረሰብ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ፍፁም፣ የሰውና ተፈጥሮ መስተጋብር ጤናማ እንዲሆን ለማስቻል ተፈጥሮን ችግኝ በመትከል መንከባከብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ክዋኔ ውስጥ ችግኝ መትከል አንዱ እንዲሆን ኪነ-ጥበብ ድርሻው ላቅ ያለ ነውም ብለዋል።
በዘንድሮ የአንድ ጀንበር የአረንጎዴ አሻራ የኪነ-ጥበቡ ማህበረሰብ አንድም ችግኝ በመትከል፤ በሙያቸው ደግሞ ይህን በጎ ተግባር በሰው ልቦና ውስጥ እንዲቀር ለዓመታት መስራታቸውን ገልፀዋል።
አቶ መሀሪ ተመስገን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ በዘንድሮ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የከተማዋ ወጣቶችና የስፖርት ቤተሰቦች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
በ11 ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ወጣቶችና የስፖርት ቤተሰቦች ሀሙስ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በነቂስ ወጥተው የራሳቸውን አሻራ እንደሚያሳርፉ ተነግ ሯል።
ወጣቶች ሊኖራቸው ከሚገቡ ነገሮች ውስጥ ጤናማና ደህንነቱ የተረጋገጠ ንፁህ አየር እንደሆነ ገልፀው፤ ጤናማ፣ ንቁ፣ ብቁ እና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ አየር ንብረቱ የተስተካከለ አገርን መረከብ አለባቸው ብለዋል።
ስለዚህ ይህንን አገር ለመስራት ወጣቱ የአንድ ጀንበር የአረንጎዴ አሻራ መርሀ ግብር ላይ በእኔነት ስሜት እንዲሳተፍ ይጠበቃል ብለዋል።
የስፖርቱ ማህበረሰብም ለእንቅስቃሴያቸው ንፁህ አየር አስፈላጊ በመሆኑ በዘንድሮ የአረንጎዴ አሻራ መርሀ ግብር እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
በዘንድሮ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የወጣቶች ማህበራት እና የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች እንደሚሳተፉ ገልፀው፤ 36 የስፖርት ማህበራት፣ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞች እና ቡድን መሪዎች በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን ያሳርፋሉ ብለዋል።
ስፖርት ማዘውተሪያዎች እና የወጣት መገንቢያዎች ችግኞች ከሚተከሉባቸው ስፍራዎች መካከል ይገኙበታል።
በሔለን ተስፋዬ