በብራዚል የሚኖሩ ጥንዶች በ20 ዓመታት ውስጥ ከ2 ሚለየን በላይ ዛፎችን በመትከል እንደገና ደንን ለመፍጠር ችለዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ 2001 ታዋቂው የፎቶ ጋዜጠኛ ሴባስቲያኦ ሳልጋዶ በሚናስ ገራይስ ግዛት በቤቱ አቅራቢያ ያለውን ጫካ የመመለስ ህልም ነበረው።
አሁን ላይ ከ20 ዓመታት በኋላ የቤተሰቡ ንብረት የብዝሃ ሕይወት ገነት ነው።
ተሸላሚው ፎቶግራፍ አንሺ እና የፎቶ ጋዜጠኛ ሴባስቲያኦ ሳልጋዶ እና ባለቤቱ ሌሊያ ዴሉዝ ዋኒክ ሳልጋዶ፣ ኢንስቲቱቶ ቴራ የተሰኘ በሀገር ደረጃ እውቅና ያለው የተፈጥሮ ጥበቃ እና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መስርተዋል።
ይህን ጥረት በ1990 አጋማሽ ላይ፣ ሳልጋዶ በሩዋንዳ የተፈፀመውን የዘር ጭፍጨፋ ከሚዘግብ የፎቶ ስራ ከተመለሰ ብዙም ሳይቆይ የጀመረው ሲሆን፣ ከባለቤቱ ጋር በመሆን በሴባስቲኦ ሳልጋዶ አባት በ1940ዎቹ ተገዝቶ በነበረው የከብት እርባታ ላይ መጀመራቸው ተዘግቧል።
ይህ መሬት በአንድ ወቅት በከብት እርባታ ምክንያት በመሸርሸር እና በደን መጨፍጨፍ ወድሞ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የደን መልሶ ማልማት ስራ በመሰራቱ ደኑን ወደ ነበረበት መመለስ ችሏል።
እነዚህ ባልና ሚስት በብራዚል በ20 ዓመታት ውስጥ ከ2 ሚሊየን በላይ ዛፎችን በመትከል 172 የአእዋፍ ዝርያዎችን፣ 33 ዓይነት አጥቢ እንስሳትን፣ 15 ዓይነት በየብስ እና በባህር የሚኖሩ እንስሳትን፣ 15 ዓይነት ተሳቢ እንስሳትን እና 293 የእፅዋት ዝርያዎችን መልሰዋል ሲል ስኑፕስ የተሰኘ ድረ-ገጽ አስነብቧል።
በቶለሳ መብራቴ