የግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብሔራዊ የግብርና ፋይናንስ ትግበራ ፍኖተ ካርታ ይፋ አደረጉ።
ፍኖተ ካርታው ከ2025 እስከ 2030 ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ተጠቁሟል።
ብሔራዊ የግብርና ፋይናንስ ትግበራ ፍኖተ ካርታው በግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ ተሳትፎን በማሻሻል ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ብሎም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል ተብሏል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ፍኖተ ካርታው ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።
የግብርናው ዘርፍ ለሀገር የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፥የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ባደረገቻቸው የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ውጤታማ ስራዎች መሥራቷን ገልጸው፤ የስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣የአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም በሌሎችም አመርቂ ስራዎች መሠራታቸውን ገልፀዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የግብርና ፋይናንስ ፍኖተ ካርታ ለግብርናው ዘርፍ ታሪካዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ጠቁመው፤ የግብርናውን ዘርፍ የፋይናንስ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የፋይናንስ ተቋማትም ከፋይናንስ አቅራቢነት ባሻገር በሁሉን አቀፍ ዕድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ የሚያስቀምጡበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ፍኖተ ካርታው ውጤታማ ትግበራ እንዲኖረውም የግብርና ሚኒስቴር ቁርጠኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፤ ፍኖተ ካርታው የፋይናንስ ተቋማት የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚሰሩ መሆኑን መናገራዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ፍኖተ ካርታው ለአርሶ አደሮች የተሳለጠ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ ያሉ ተዋናዮች ሁሉን አቀፍ፣የበለፀገ እና ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ምቹ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሚሰራም ጠቁመዋል።