ከአለም ስኬታማ የደን መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች መካከል በጥቂቱ :-
ታላቁ አረንጓዴ ግድግዳ (The Great Green Wall) – አፍሪካ
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት 11 የአፍሪካ ሳህል ክልል እና የአፍሪካ ቀንድ ሃገራትን በዋናነት ያሳተፈ ነው።
እ.ኤ.አ በ2007 በአፍሪካ ህብረት የተጀመረው ፕሮጀክት በአየር ንብረት ለውጥ እና ከመጠን ያለፈ መጠቀም ምክንያት ለበረሃነት የተጋለጠን 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት፤ በ2030 የደን ሽፋኑን ለመመለስ እና በቀጠናው ኑሮን ለማሻሻል ያለመ ነው።
ፕሮጀክቱ ከሴኔጋል አንስቶ እስከ ጅቡቲ የሚደርስ 8 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 15 ሺህ ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍን የአረንጓዴ ሞዛይክ የሚፈጥር ነው።
ይህንን ፕሮጀክት ለመደገፍ ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተሰብስቧል። እስካሁን ከእቅዱ 20 ሚሊዮን ሄክታርን በደን መሸፈን ተችሏል።
ሶስት – ሰሜን የመጠለያ ቀበቶ (Three-North Shelter Forest Program ) – ቻይና
በፈረንጆቹ 1978 ተጀምሮ በ2024 የተጠናቀቀው የቻይና ታላቁ አረንጓዴ ግድግዳ በትልቁ ታክላማካን በረሃ ዙሪያ 3 ሺህ ኪ.ሜ የሚሸፍን የ88 ቢሊዮን ዛፎች አረንጓዴ ቀበቶን በመፍጠር የተጠናቀቀ ነው።
በረሃማነትን ለመከላከል እና በፀደይ ወቅት የሚነሳውን የአሸዋ አውሎ ነፋስ ለመከላከል ታቅዶ በተጀመረው ሃገራዊ ፕሮጀክቱ ከ30 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬትን በደን መሸፈን ተችሏል።
ፕሮጀክቱ ሃገሪቱን አጠቃላይ የደን ሽፋን ከ10 በመቶ ወደ 25 በመቶ ለማሳደግ አስተዋፅኦ አድርጓል።
የደን ሽፋንን ከ17 በመቶ ወደ 54 በመቶ – ኮስታሪካ፡
በፈረንጆቹ 1970 የደን ሽፋናቸው ዝቅተኛ ነው ከተባሉት ሃገራት መካከል የሆነችው ኮስታሪካ ለአስርት ዓመታት በቆየው ጠንካራ የስነ-ምህዳር ፖሊሲ የደን ሽፋኗን ከ17 በመቶ በ2024 ወደ 54 በመቶ ማሳደግ ችላለች።
ለመሬት ባለይዞታዎች ለደን መልሶ ማልማት እና መንከባከብ ማካካሻ ክፍያን በመፈፀም በተገበረችው ፖሊሲ፤ አሁን ከካርበን ነፃ ሃገር መሆን ችላለች።
በሊያት ካሳሁን