የሀገር ሽማግሌዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዘብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ትግራይ ክልል በመሄድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የሚመለከታቸውን የፌደራል መንግሥት የሥራ ሀላፊዎችን ለማነጋገር ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ከሰላም ሚኒስትርና ከሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱም የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሀመድ ኢድሪስ ከሁሉም ክልሎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡት የሀገር ሽማግሌዎች በራሳቸው ተነሻሽነት ተደራጅተው ሰላም ከማስፈን አንጻር የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን አድንቀው በኢትዮጵያዊ ሀገራዊ ባህልና እሴት ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
መንግሥት በትግራይ ክልል አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተው የትግራይ ክልል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ሳይስተጓጎሉ እንዲቀጥሉ በርካታ ሥራዎችን መስራቱን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኛ አቋም በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቀየቱንና ለወደፊትም ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልጸው መሰል ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡